የኢትዮጵያ የወርቅ ማዕድን ዘርፍ ከፍተኛ አደጋ ከሚታይበት አሰራር ወጥቶ ለሀገር ኢኮኖሚ ስትራቴጂካዊ ምሰሶ እንዲሆን የሚያስችለውን የተባበሩት መንግስታት ድጋፍ ያገኘ የደህንነት ፕሮቶኮል (መስፈርት) ተግባራዊ እያደረገ መሆኑ ተገለጸ።
ይህ ለውጥ የመጣው የሜድሮክ ወርቅ ማዕድን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያለውን የሳይያናይድ አጠቃቀም ደህንነት መመሪያ በማሟላት በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የተረጋገጠ ድርጅት ሆኖ በመመዝገቡ ነው።
በተባበሩት መንግስታት የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም ድጋፍ የወጣው ይህ መመሪያ፣ ወርቅን ለማውጣት ጥቅም ላይ የሚውለውን ሳይያናይድ ደህንነቱ በተጠበቀ ሁኔታ ለማጓጓዝ እና ለመጠቀም የሚረዳ ዓለም አቀፍ ደረጃ ነው።
የዓለም አቀፍ የሳይያናይድ ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ሰብሳቢ ፖል ባትማን እንደገለጹት፤ የሚድሮክ ለገደንቢ ወርቅ ማዕድን ይህንን የምስክር ወረቀት ማግኘቱ ለሌሎች የማዕድን ኩባንያዎች እንደ አርአያ የሚጠቀስ ነዉ።
ከሰሞኑ በአዲስ አበባ በተካሄደው ዓለም አቀፍ የምክክር መድረክ ላይ እንደተጠቀሰው፣ የማዕድን ዘርፉ ዘላቂ ሊሆን የሚችለው የአካባቢ ጥበቃ እና የሰዎች ደህንነት ሲጠበቅ ብቻ ነው።
እነዚህን ዓለም አቀፍ መስፈርቶች ተግባራዊ ማድረግ ከአደጋ መከላከል ባለፈ የላቀ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያለው ሲሆን፣ በቡድን 8 እና በሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት ዕውቅና የተሰጣቸውን ደህንነቶች መተግበር የኢትዮጵያ ወርቅ በዓለም ገበያ ተፈላጊ እንዲሆን እና የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ትልቅ ዕድል ይፈጥራል ተብሏል።
ይህ አሰራር ዓለም አቀፍ ተዓማኒነትን ከመገንባቱ ባለፈ፣ ባለፉት 20 ዓመታት ውስጥ መስፈርቱን ባሟሉ ቦታዎች ላይ ምንም ዓይነት የሞት አደጋ አለመመዝገቡን ተከትሎ በዘርፉ የሚከሰቱ የአካባቢ እና የጤና ችግሮችን በእጅጉ ይቀንሳል።
በተጨማሪም በአካባቢው የሚኖሩ ማህበረሰቦችን እና ተፈጥሮን ከኬሚካል ብክለት መጠበቅ፣ በማዕድን ኩባንያዎች እና በነዋሪዎች መካከል ሰላማዊ ግንኙነት እንዲኖር በማድረግ የምርት ሂደቱ ሳይስተጓጎል እንዲቀጥልና ለሀገር መረጋጋት አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ይረዳል።
ከ12 ሀገራት የተውጣጡ ተወካዮች የተሳተፉበትና በአዲስ አበባ የተካሄደው ዓለም አቀፍ ወርክሾፕ እንደሚያመለክተው፣ የሚድሮክ ስኬት የኢትዮጵያን የማዕድን ደህንነት ለማስፋፋት እንደ መነሻ ተወስዷል።
ፖል ቤትማን እንደገለጹት፣ ዓላማው ይህንን የደህንነት አሰራር ወደ ሌሎች የማዕድን ኩባንያዎች፣ የትራንስፖርት ድርጅቶች እና የኬሚካል አምራቾች በማስፋፋት የሰራተኞችን፣ የማህበረሰቡን እና የሀገርን ጥቅም ማረጋገጥ ነው።
