እናት ፓርቲ ” መነጠላችን ቢያስቆጭም መመለሳችን ለትግሉ አቅም ነው ” ሲል ወደ ትብብሩ መመለሱን አመልክቶ መግለጫ አዉጥቷል።
እናት ፓርቲ የተበታተነ የተናጠል ትግል ውጤት እንደማያመጣ በማመን ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር በጋራ በትብብር ለመስራት ጥሪ ሲያደርግ ጥረትም ሲያደርግ መቆየቱን ገልጿል።
በሂደት የተወሰነው ተንጠባጥቦ የተወሰነው ወደስልታዊ ትብብር መምጣቱን አመልክቷል።
” ልብ ለልብ የተዋወቁና ከፓርቲና ግለሰብ ፍላጎት ይልቅ የአገራቸው ነገ ያገበራቸው ፓርቲዎች ቆይቶም ወደሕጋዊ ቅንጅት አድገው መምጣታቸውን ” አስታውሷል።
በኋላም ” የሚታወቁ ” ያላቸው መሰናክሎች ገጥሞት ፓርቲው ከቅንጅቱ ተገልሎ እንደነበር ገልጿል።
አሁን ላይ ፓርቲው ወደቅንጅቱ (ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት-ኢትዮጵያ) መመለሱን በታላቅ ደስታ አብስሯል።
” የትብብራችን ልባዊ ግንኙነት ኢትዮጵያውያንን ለሰላማዊ ትግል ለማስተባበርና ለመምራት አቅም ይሆናል የሚል ጽኑ ዕምነት አለን ” ብሏል።
” ሂደቱ ከእነእድካሚነቱ ከተጣለበት ተነስቶ ነፍስ እንዲዘራና ሕልው እንዲሆን የፓርቲያቸን የምክር ቤት አባላት እየተዛተባቸውና እየተንጓጠጡ ጭምር ላሳዩት በሳል አመራር ከፍ ያለ ምሥጋና ይገባቸዋል ” ሲል ገልጿል።
የቅንጅቱ አመራሮችና አንዳንድ ቅን ኢትዮጵያውያን ያሳዩትን አጋርነት ብርታት እንደሆነው በማመልከት አመስግኗል።
እናት ፓርቲ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አመራሮችንም አመስግኗል።
” የሂደቱ መደናቀፍ ያለውን ጉዳት ተረድተው ለሰጡት በሳል አመራርና ያላሰለሰ ጥረት እውቅና እንሰጣለን፤ ምሥጋናም ለማቅረብ እንወዳለን ” ብሏል።
