ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት ሚዲያዎችን የመዝጋት ተግባር እንዲቆም አሳሰበ

Date:

ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት የተሰኘው የፖለቲካ ድርጅቶች ቅንጅት፣ በ አማራ፣ ኦሮሚያ፣ ትግራይ እና በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎችና በታጠቁ ቡድኖች መካከል የሚካሄደው ግጭት በንጹኃን ዜጎች ላይ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን ገለጸ።

ቅንጅቱ፤ መንግስት በገለልተኛ ዘገባና የሕዝብ ድምጽ በመኾን የሚታወቁ ሚዲያዎችን እየዘጋ፣ የጋዜጠኞቻቸውንም ፈቃድ እየነጠቀ መሆኑን ገልጾ፤ የእርምት እርምጃ እንዲወስድ አሳስቧል።

ኢሕአፓ እና እናት ፓርቲን በአባልነት የያዘው ቅንጅቱ የካቲት 20 ቀን 2018 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ፣ ባለፉት ሰባት ዓመታት ሀገሪቱ የገባችበት የጦርነት ዑደት ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሶ፣ በተለይ በአማራ ክልል በንጹኃን ላይ እየተፈጸመ ያለው ጥቃት አሳሳቢ መሆኑን አመልክቷል።

በአማራ ክልል በደቡብ ወሎ ዞን ወግዲ ወረዳ፣ በሰሜን ሸዋ ኤፍራታና ግድም ወረዳዎች እንዲሁም በደቡብ ጎንደር ደብረ ታቦርና ወረታ ከተሞች በቅርብ ቀናት ውስጥ በተፈጸሙ የድሮንና የከባድ መሣሪያ ጥቃቶች ንጹኃን መገደላቸውን ድርጅቱ ገልጿል።

በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ አርሲ መርቲ ወረዳና በሰሜን ሸዋ ወራጃርሶ ወረዳ ሃይማኖትና ማንነትን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች መፈጸማቸውን የጠቀሰው ቅንጅቱ፣ መንግሥት ዜጎችን የመጠበቅ ኃላፊነቱን እንዲወጣ አሳስቧል።

በትግራይ ክልል ያለው ሁኔታም አሳሳቢ መሆኑን የጠቀሰው መግለጫው፣ ዳግም ወደ ጦርነት እንዳይገባ ሁሉም ወገኖች እንዲታቀቡና የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ አስፈላጊውን ጥረት እንዲያደርግ ጥሪ አቅርቧል።

በተጨማሪም መንግሥት ነፃና ገለልተኛ ሚዲያዎችን መዝጋቱንና የጋዜጠኞችን የሥራ ፈቃድ መንጠቁን ድርጅቱ ተቃውሟል።  መንግስት በአንጻራዊነት በገለልተኛ ዘገባና የሕዝብ ድምጽ በመኾን የሚታወቁ ሚዲያዎችን እየዘጋ፣ የጋዜጠኞቻቸውንም ፈቃድ እየነጠቀ ይገኛል ያለው ቅንጅቱ፤ “ትግበራውም ግልጽነት የጎደለውና ከብሔራዊ ጥቅም ወይም ከሕዝብ ደህንነት አንጻር የተቃኜ ሳይኾን የሚፈጽመው ግፍ እንዳይጋለጥ ከመፍራት የመነጨ ነው” ብሏል።

እንዲኽ ያለው ድርጊት ከዓለምአቀፍ መርኆዎች እንዲሁም ከሕገ መንግሥት ድንጋጌም የሚጣረስ በመኾኑ መንግሥት የሕዝብን በነጻነት መረጃ የማግኘት መብት አክብሮ እንዲንቀሳቀስና ተገቢውን የእርምት እርምጃ እንዲወስድ አሳስቧል።

https://addisstandard.com/Amharic/?p=11006

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

አክሊሉ ወንድሞቹ ለንባብ በቃ

በፀሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ የልጅነት ታሪክ ላይ ያተኮረ ለታዳጊዎች...

የኢራን ተፈጥሮአዊ ምሽጎች እና ስትራቴጂካዊ ጥበብ

​ግዮን መጽሔት :- በመካከለኛው ምስራቅ የጂኦ-ፖለቲካ ትኩሳት...

ለአድዋ ድል መታሰቢያ በአሜሪካ ቀን ተሰየመ

በአሜሪካ፣ የፔንሲልቪኒያ ግዛት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ የአውሮፓዊያኑ 'መጋቢት...

ኢሎን መስክ የዓለማችን የመጀመሪያው ትሪሊዮነር ሆነ

ኢሎን መስክ የሀብት መጠኑ 1 ትሪሊዮን ዶላር ያለፈ የመጀመሪያው...