የኢትዮጵያ ማረሚያ ኮሌጅን የድህረ ምረቃ ዲፕሎማ ትምህርት ለማስጀመር በኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ሲዘጋጅ የቆየው ካሪኩለምና ሞጁል ስራ ተጠናቆ የፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን በይፋ ተረክቧል።
ኮሌጁን ስራ ለማስጀመር የሚያስችሉ ሰነዶችን የተረከቡት የፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀኔራል የኑስ ሙሉ በአስተላለፉት መልዕክት የማረሚያ ሳይንስ ትምህርት በሃገራችን ብዙ እንዳልተሰራበት ገልጸው፣ ነገር ግን የየዕለት ስራዎች ጽናትን፣ ርህራሄን፣ ሰዎችን መርዳትንና ራስን አሳልፎ መስጠትን የሚጠይቁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ኮሚሽነር ጄኔራሉ አክለውም ኮሚሽኑ የተረከባቸው ሰነዶች በድህረ ምረቃ ዲፕሎማ ትምህርት በመጀመር በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል በማፍራት በፌዴራልና በክልል ማረሚያ ቤቶች ያለውን የሰው ኃይል ክፍተት ለመሙላት በከፍተኛ ደረጃ ያግዛሉ ብለዋል፡፡
ሰነዶችን ያስረከቡት የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርስቲ ፕሬዘዳንት ዶ/ር ታምራት ሙሉጌታም በአስተላለፉት መልዕክት የፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽንን በተማረ የሰው ኃይል ለማጠናከር በዘርፉ የተሻለ ዕውቀትና ግንዛቤ ባላቸው ባለሙያዎች የኮሌጁ ስርዓተ ትምህርት በጥራት መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡
