በአውሮፓ ህብረት እና በኢትዮጵያ መካከል በሚካሄደው የንግድ ፎረም መክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ፣ የአውሮፓ ህብረት ከአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና ሴክሬታሪያት ጋር የመግባቢያ ሰነድ ሰኞ ዕለት እንደሚፈራረም ታውቋል።
ሚያዚያ 12 ቀን 2018 ዓ.ም. የሚደረገዉ ይህ ስምምነት የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን እና ስምንት አባል ሀገራት በጋራ የሚያከናውኑት የ“ቲም ዩሮፕ ኢንሼቲቭ” አካል ሲሆን፣ በአጠቃላይ 1.2 ቢሊዮን ዩሮ የሚገመት በጀት ተመድቦለታል።
ጥምረቱ እነዚህ የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራትን ማለትም (ዴንማርክ፣ ጀርመን፣ አየርላንድ፣ ፈረንሳይ፣ ኔዘርላንድስ፣ ፊንላንድ፣ ፖርቹጋል እና ስዊድን) በአንድ ላይ ያሰባሰበ ነው።
በአሁኑ ወቅት ከ80 በላይ ንቁ ፕሮጀክቶችን በአባልነቱ የያዘው ይህ ኢኒሼቲቭ፣ የአውሮፓ ህብረት ለአፍሪካ ኢኮኖሚያዊ ውህደት ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑ ተመላክቷል።
የስምምነቱ ዋነኛ ዓላማ የአፍሪካን ኢኮኖሚያዊ ውህደት መደገፍ እና የአህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነትን ወደ ተግባር ለማሸጋገር የሚደረገውን ጥረት በገንዘብና በቴክኒክ ማገዝ መሆኑ ተጠቁሟል።
capital news
