ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወኃት)ከኤርትራ እና ከሱዳን ጋር በጋራ እየሠራ ነው በማለት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሰነዘሩበትን ክስ ውድቅ አደረገ።
ቡድኑ ከየትኛውም የውጭ አካል ወታደራዊ ድጋፍ እንደማይፈልግ እና «በራሱ ኃይል እንደሚተማመን» ገልጿል።
ይህ ምላሽ የተሰጠው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ባለፈው ማክሰኞ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ ላይ፥ ሱዳን፣ ሕወኃት እና ኤርትራ በጋራ እየሠሩ መሆኑን በመጥቀስ፤ ይህንን ሁኔታ እ.ኤ.አ. በ1991 የደርግ ሥርዓት እንዲወድቅ ካደረገው ጥምረት ጋር በማመሳሰል ከሰጡት አስተያየት በኋላ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህ ጥምረት በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ላይ የሚያመጣው አደጋ የለም ሲሉ ተናግረዋል። ነገር ግን ስማቸውን ያልጠቀሷቸው የውጭ አካላት ከጀርባ ሆነው እየመሩት መሆኑን ጠቁመዋል።
ለእነዚህ ክሶች ምላሽ የሰጡት የሕወኃት ቃል አቀባይ ሚካኤል አስገዶም፤ ድርጅታቸው አብረውት ተሰልፈው እንዲዋጉለት የውጭ አካላትን በፍጹም ጋብዞ አያውቅም ብለዋል።
