የኤካ ኮተቤ ሆስፒታል ለክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት 30 ሚልዮን ብር የሚያወጣ ህክምና ለ200 ሺህ ዜጎች በነጻ መስጠት መጀመሩን አስታውቋል።
የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ረድኤት ሰለሞን እንደገለጹት፤ ፕሮግራሙ በየካ ክፍለ ከተማ ግቢ ውስጥ ዛሬ በይፋ ተጀምሯል።
የነጻ ሕክምና አገልግሎቱ ለ10 ቀናት የሚቆይ ሲሆን እስከ ሐምሌ 17 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ ይቆያል ተብሏል።
ከሚሰጡት አገግሎቶች መካከል፦ የውስጥ ደዌ፣ የቀዶ ሕክምና፣ የዓይን፣ የጥርስ፣ የቆዳ እና የአዕምሮ ሕክምና አገልግሎቶች ይገኙበታል።
የሕጻናት፣ የማኅፀንና ፅንስ ሕክምናዎችን ጨምሮ አንገት በላይ ሕክምናዎችም ተካተዋል ተብሏል።
ለሕክምናው የሚያስፈልጉ መድኃኒቶች እና የላብራቶሪ ምርመራዎች በነጻ እንደሚቀርቡም ተገልጿል።
ዶክተር ረድኤት እንደተናገሩት፤ ክትትል የሚያስፈልጋቸው ወይም ከተቋሙ አቅም በላይ የሆኑ ሕመምተኞች ወደ ተመረጡ የሕክምና ተቋማት በሪፈር ይላካሉ።
ባለፈው ዓመታት በተደረገው የነጻ ምርመራ የስኳር፣ የደም ግፊት፣ የካንሰር እና የአዕምሮ ህመምተኞች መለየታቸውን ጠቁመዋል።
የክረምት በጎ አድራጎት ሥራውን ሆስፒታሉ ለሦስተኛ ዓመት እያከናወነው ሲሆን፤ ባለፈው ዓመት ለ195 ሺህ ሰዎች የነጻ ሕክምና አገልግሎት መስጠታቸውን ዳይሬክተሯ አስታውሰዋል።
ማናቸውም ዜጋ የነጻ ምርመራውን በማድረግ ተጠቃሚ መሆን እንደሚችልም ተገልጿል።
