ኢራን በዮርዳኖስ በፈጸመችው ጥቃት ሁለት የአሜሪካ ወታደሮች ሲገደሉ አንዱ የደረሰበት አልታወቀም

Date:

ኢራን አርብ ዕለት ዮርዳኖስ ውስጥ በፈጸመችው የባለስቲክ ሚሳዔል እና የድሮን ጥቃት፤ ሁለት የአሜሪካ መከላከያ ሠራዊት አባላት እንደተገደሉ እና አንዱ ደግሞ እስካሁን የደረሰበት እንደማይታወቅ የሠራዊት ባለሥልጣናት ገለጹ።

አራት የአሜሪካ ወታደሮች ለሕክምና ዮርዳኖስ ውስጥ ወደሚገኙ ሆስፒታሎች ከተወሰዱ በኋላ እርዳታ አግኝተው መውጣታቸውን የአሜሪካ ጦር ማዕከላዊ ዕዝ (ሴንትኮም) አስታውቋል።

ቀላል ጉዳት የደረሰባቸው ሌሎች የሠራዊቱ አባላት ደግሞ ወደ ሥራቸው መመለሳቸው ተነግሯል።

የአሜሪካ ወታደራዊ ባለሥልጣናት የተገደሉትን ወታደሮች ማንነት፣ የጥቃቱን ዝርዝር መረጃ እንዲሁም ክስተቱ ያጋጠመበትን ትክክለኛ ቦታ ይፋ አላደረጉም።

ይሁን እንጂ ቅዳሜ ምሽት የአሜሪካ ጦር በፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ትዕዛዝ ኢራን ላይ ሌላ ዙር ጥቃት መፈጸሙን ማዕከላዊ ዕዙ አስታውቋል።

ለስምንተኛ ተከታታይ ምሽት የተፈጸመው ጥቃት፤ “ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ የሚጓዙ የንግድ መርከቦች ላይ ያላትን ስጋት የመፍጠር አቅም ይበልጥ ለማዳከም ያለመ” እንደሆነ ዕዙ ገልጿል።

ጥቃቶቹ “ትናንት ምሽት ዮርዳኖስ ውስጥ የአሜሪካ ሠራዊት አባላት ላይ ጥቃቶችን የከፈቱትን የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ኃይሎች በቶሎ ለመቅጣት” ያለሙ እንደነበሩም አስታውቋል። ስለ ጥቃቶቹ ግን ዝርዝር መረጃ አልገለጸም።

የካቲት ላይ በተነሳው በዚህ ጦርነት የተገደሉ የአሜሪካ የሠራዊት አባላት ቁጥር 16 ደርሷል። በዚህ ወር የት እንደደረሰ መጥፋቱ የተነገረው የባሕር ኃይል ፓይለት ሕይወቱ እንዳለፈ ተገልጿል።

ሴተትኮም ቅዳሜ ዕለት ባወጣው መግለጫ፤ “የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ እና አጋር ኃይሎች የኢራንን የባለስቲክ ሚሳዔል እና የድሮን ጥቃቶችን እየተከላከሉ በነበረበት ሰዓት ዮርዳኖስ ውስጥ ሁለት የአሜሪካ የሠራዊት አባላት በውጊያ ላይ ተገድለዋል። በተጨማሪም በአሁኑ ሰዓት አንድ ወታደር ጠፍቷል” ብሏል።

“ለቤተሰቦቻቸው ክብር ሲባል፤ በሚቀጥሉት 24 ሰዓታት ውስጥ ዘመዶቻቸው እስከሚነገራቸው ድረስ ማዕከላዊ ዕዙ የተዋደቁትን ተዋጊዎች ማንነት ጨምሮ ዝርዝር መረጃ ከመግለጽ ተቆጥቧል” ሲል በመግለጫው አስፍሯል።

የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ በበኩሉ፤ ቅዳሜ ዕለት ዮርዳኖስ ውስጥ በሚገኘው አል አዝራቅ የጦር ሰፈር በፈጸመው ጥቃት ቢያንስ ሁለት የአሜሪካ የጦር አውሮፕላኖችን ማውደሙን እንደገለጸ የአገሪቱ መንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ ስለዚህ ጥቃት ተጨማሪ መረጃ እንዲሰጥ ከቢቢሲ የቀረበለትን ጥያቄ ውድቅ አድርጓል።

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

ጄኤፍኤም 106.7 የሬዲዮ ጣቢያ ለ6 ወራት ታገደ

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ባደረገው የይዘት ክትትልና የኢንስፔክሽን ምልከታ...

ሱልጣን ቢን ኻሊፋ ግሩፕ በኢትዮጵያ በሆቴል ዘርፍ ሊሰማራ ነው

በተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች የኢፌዲሪ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር...

የአሜሪካ የታክስ ህግ የስፔንን የዓለም ዋንጫ ሽልማት ስጋት ላይ ጣለ

የስፔን ብሔራዊ ቡድን ከዓለም ዋንጫ ሊያገኘው ከሚችለው 50 ሚሊዮን...

ህወሓት ከሌሎች ተቃዋሚ ኃይሎች ጋር የሚደረግ ጥምረት አስፈላጊ መሆኑን ገለጸ

ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ...