ላለፉት 93 ዓመታት በዘርፉ የሰራው የዳግማዊ ምኒልክ መታሰቢያ የመምህራን እና ቀሳውስት ማሰልጠኛ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት፣ በተለያዩ የትምህርት ክፍሎች ለ2 ዓመታት ያሰለጠናቸውን 183 ተማሪዎች በዲፕሎማ እና በሰርቲፊኬት አስመርቋል።
ተመራቂዎቹ የመጽሐፍት ትርጓሜ፣ ቅኔ፣ ድጓ፣ ቅዳሴ እና ንባብን ጨምሮ በ8 የትምህርት ዘርፎች የሰለጠኑ ናቸው።
ከአጠቃላይ ተመራቂዎች መካከል 70 ያህሉ በአብነት ትምህርት ስር የተካተቱ ሲሆኑ፣ ቀሪዎቹ በቅዳሜ እና እሁድ መርኃ-ግብር ለሁለት ዓመታት የሰለጠኑ መሆናቸውን የትምህርት ቤቱ መረጃ ያመለክታል።
የበዓታ ለማርያም ቤተ-ክርስቲያን እና የትምህርት ቤቱ አስተዳዳሪ ሊቀ ሊቃውንት አባ ተክለ ሃይማኖት ወልዱ እንደገለጹት፤ ትምህርት ቤቱ የመጽሐፍ ቅዱስን እና ሌሎች መንፈሳዊ ትምህርቶችን ለሰፊው ምዕመን ለማዳረስ ስራዎችን ጀምሯል።
ተቋሙ ተደራሽነቱን ለማስፋት በሚያደርገው ጥረት፣ ሁሉም ምዕመን በትምህርት ቤቱ ግንባታ ላይ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያደርግ አስተዳዳሪው ጥሪ አቅርበዋል።
ትምህርት ቤቱ በንግሥተ-ነገሥታት ዘውዲቱ ዘመነ መንግሥት ተጀምሮ፣ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን መጠናቀቁ ይታወሳል።
የጥንታዊ ትምህርት ቤቱን አቅም በማሳደግ መንፈሳዊ ዕውቀትን ለምዕመናን የማድረስ ስራ በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተመላክቷል።
