ጅቡቲ ሕገ ወጥ የምትላቸው ስደተኞችን በቅርቡ ማባረር እንደምትጀምር አስታወቀች።
የጅቡቲ ፕሬዝዳንት ኢስማኤል ኦማር ጉሌህ አማካሪን ጠቅሶ የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት እንደዘገበው ጅቡቲ የሚገኙ ሕገ ወጥ ስደተኞች በሚያዚያ መጨረሻ ማለት ባንድ ሳምንት ዉስጥ ሀገሪቱን ለቀው እንዲወጡ የሀገሪቱ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር አዟል።
ውሳኔውም በዋነኛነት የፀጥታ እና የጤና ስጋቶችን መነሻ ያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።
አማካሪው በጅቡቲ ምን ያህል ሕገ ወጥ ስደተኞች እንዳሉ ግን አልተናገሩም።
ጅቡቲ ለበርካታ የኢትዮጵያ፣ የሶማሊያና የኤርትራ ስደተኞች ወደ ሃብታሞቹ የመካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት መሸጋገሪያ ናት።
የተመድ እንዳስታወቀው በጎርጎሮሳዊው 2024 ብቻ በጅቡቲ አድርገው ወደ ሌሎች ሀገራት ለመሻገር የሞከሩ ቢያንስ የ558 ስደተኞች ህይወት አልፏል።
በጅቡቲ ሕጋዊ የመኖሪያ ሰነድ የሌላቸው ኢትዮጵያውያን እና የሌሎች ሀገራት ዜጎች ወደየሀገራቸው የመመለሻ ጊዜ አለመራዘሙን በጅቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ማስታወቁ የሚታወስ ነው።
