ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በተያዘለት የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቅ እና ቀሪ ተርባይኖች ሀይል እንዲያመነጩ ለማድረግ ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ የሚገኝ ሲሆን፤ የቦንድ ሽያጭን ጨምሮ ሌሎችም የገቢ ማሰባሰቢያ መርሀግብሮች ተጠናክረው መቀጠላቸው የሕዳሴ ግድብ ማስተ ባበሪያ ጽ/ቤት ለአሐዱ አስታውቋል።
ግንባታው ከ97 ነጥብ 6 በመቶ በላይ እንደደረሰና ጥቂት የማጠናቀቂያ ሥራዎች ብቻ እንደቀሩት ለአሐዱ የተናገሩት፤ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ፅህፈት የፐብሊክ ዲፕሎማሲና ሕዝብ ግንኙነት ሥራ አስፈፃሚ ሰለሞን ዳንኤል ናቸው፡፡
በዚህም ግድቡን በስድስት ወራት ውስጥ ለማጠናቀቅ የቴክኒክ ሥራዎች፣ የቦንድ ሽያጭ፣ የየዲያስፖራ ድጋፍ እና የበጎ ፍቃደኞች የገንዘብ ድጋፎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን የተናገሩት ኃላፊው፤ ወደሥራ ያልገቡ ዩኒቶችም እንዲሁ በተቀመጠላቸው እቅድ መሠረት ተራ በተራ ወደ ኃይል ምርት ለማስገባት ርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ከፋይናንስ ጋር በተያያዘም በቦንድ ግዢ እና በሌሎች የገንዘብ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብሮች በሰባት ወራት ውስጥ ብቻ ከ780 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን ገልጸው፤ በአጠቃላይ ግን 21 ቢሊዮን 666 ሚሊዮን ብር መሰብሰብ መቻሉን ተናግረዋል።
አክለውም ለሕዳሴው ግድብ ገቢ ለማሰባሰብ በየክልሉ ሲዞር የነበረው ዋንጫም ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
የግንባታው የመሠረት ድንጋይ በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ መጋቢት 24 ቀን 2003 የተጣለው የሕዳሴው ግድብ ባለፈው ወር 14 ዓመት ሞልቶታል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መጋቢት 11 ቀን 2017 ዓ.ም. የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት የአፈጻጸም ሪፖርት መነሻ በማድረግ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት ወቅት፤ “በሚቀጥሉት ስድስት ወራት የታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ሪቫን ቆርጠን ታሪክ እናደርገዋለን” ማለታቸው ይታወሳል።
በፅዮን ይልማ
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
