የእስራኤል የጸጥታ ካቢኔ ያወጣው አዲስ እቅድ በሃማስ ላይ ወታደራዊ ጥቃት በማስፋፋት ጋዛን “መያዝ” ይጨምራል ሲሉ የእስራኤል ባለስልጣን መናገራቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የካቢኔው ምክር ቤት ሃማስን ለማጥፋት እና የተቀሩትን ታጋቾች ለመታደግ “ጠንካራ እርምጃ” ይወስዳል፡፡2.1 ሚሊዮን የጋዛ ህዝብንም “ከአደጋ ለመጠበቅ ይንቀሳቀሳል” ብለዋል።
ምን ያህል ግዛት በእስራኤል ወታደሮች እንደሚወሰድ ባይገልጽም “አይገቡም አይወጡም” ሲሉ አሳስበዋል።
ካቢኔው በመርህ ደረጃ ዕርዳታን በግል ኩባንያዎች ለማድረስ የተያዘውን እቅድ አጽድቆ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከፍተኛ የምግብ እጥረት አስከትሏል ያለውን የሁለት ወራት እገዳ ይቀርፋል ተብሏል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና ሌሎች የእርዳታ ድርጅቶች ሃሳቡ መሰረታዊ የሰብአዊ መርሆችን መጣስ እንደሚሆን እና እንደማይተባበሩም ተናግረዋል።
የሃማስ ባለስልጣን የእስራኤልን “ግፊት እና ወሳኔ” ውድቅ አድርጓል።
