ከአዲስ አበባ ወደ ተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች እና ክልሎች የሚንቀሳቀሱ የትራንስፖርት ተገልጋዮች ቀድሞ ከነበረው ታሪፍ 2 መቶ እና ከዛ በላይ ክፍያ ጭማሪ እንደሚጠየቁ ለአሐዱ ቅሬታቸውን አሰምተዋል፡፡
ከላምበረት እና አየር ጤና መናህሪያ ከመነሻው ትክክለኛውን ክፍያ ከከፈሉ በኃላ አዲስ አበባ መውጫ አካባቢ ላይ ተጨማሪ ክፍያን እንዲከፍሉ መገደዳቸውን ተገልጋዮቹ ተናግረዋል፡፡
የትራንስፖርት ጭማሪው ያማረራቸው ተገልጋዮች ለያዙት ንብረት እና እቃ ተጨመሪ ክፍያ እየተጠየቁ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
አሐዱም ይህንን ጉዳይ በተመለከተ የትራንስፓርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር የትራንስፖርት አገልግሎትና ቁጥጥር ዘርፍ አማካሪ አቶ አሰፋ ሀዲስን ጠይቋል፡፡
በምላሻቸውም ከመመሪያ ውጭ ያልተገባ ክፍያ በሚያስፈክሉ አሽከርካሪዎች ላይ ከፍተኛ ቁጥጥር እየተደረገ እና እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በተጨማሪም ማህበረሰቡን አላስፈላጊ ወጭ የሚዳርጉ አሽከርካሪዎች እና የንብረቱ ባለቤቶች ተጠያቂ እንዲሆኑ ጥቆማ መስጠት እንደሚያስፍልግ አንስተው ተቆጣጣሪዎችን በየክልሎች በመመደብ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
እንደዚህ አይነት ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ ለሚመለከተው አካል ጥቆማ መስጠት እንደሚያስፈልግ የትራንስፓርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር አሳስቧል፡፡
(አሐዱ ሬድዮ)
