ጥንታዊቷ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መልከ ብዙ በሚባል ፈተናዎች ውስጥ እያለፈች ነው፡፡ በርግጥ የሃይማኖቱ አባቶች እንደሚናገሩት ክርስትና ከመከራ የተለየ ታሪክ እና መገለጫ ኖሮት አያውቅም፡፡ ያም ኾኖ ግን በኢትዮጵያ አሁናዊ ተጨባጭ ሁኔታ ቤተ ክርስቲያኒቱ የጥቃት እና የፍረጃ ዒላማ የኾነችበት አመክንዮ የዚህ መገለጫዋ ውጤት ተደርጎ ብቻ ሊወሰድ አይችልም፡፡ ከሌሎች የመካከለኛው ምሥራቅ እና የአውሮፓ ሀገራት በተለየ ኢትዮጵያ ውስጥ ክርስትና ለሺህ ዘመናት የነበረውን ሥፍራ ላጤነ ደግሞ ፈተናው ባለፉት ጥቂት ዐሥርት ዓመታት ገፍቶ የመምጣቱ ምክንያት ሌላ መልክ ኖሮት ያገኛል፡፡
በተለይም ደግሞ የጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ኮርቻው መምጣትን ተከትሎ ባለፉት አምስት ዓመታት ቤተ ክርስቲያኒቷ ላይ የደረሱ መከራዎች በዐይነትም በቅርጽም እየተለዩ መምጣታቸው የዕምነቱን ተከታዮችን ብቻ ሳይኾን ሌሎች ኢትዮጵያውያንንም ጭምር ሥጋት ላይ ጥሏል፡፡ ይኽ አልበቃ ብሎ ጥር 14 ቀን 2015 ዓ.ም ግልጽ በኾነ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት የቤተ ክርስቲያኒቱን ሕጋዊ እና ተቋማዊ መዋቅር በናደ መልኩ የተፈጸመው ‹‹ሢመት›› ደግሞ መከራውን ወደ ሌላ ምዕራፍ አሻግሮታል፡፡ በዚህም ሳቢያ መንግሥት የተፈጠረውን ኢ-ቀኖናዊ አካሔድ በኃይል ለመፍታት ሲሞክር ያደረሰው የሰው እና የንብረት ጉዳት፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ በታሪኳ ካጋጠሟት ፈተናዎች የተለየ ኾኖ እንዲመዘገብ ምክንያት ኾኗል፡፡
ከዚያ በኋላ ባሉት ጊዜያትም ቢኾን መንግሥት ፍላጎቱን በኃይል ለማስፈጸም የሔደበት ርቀት አለመሳካቱን ተከትሎ፣ ቤተ ክርስቲያኒቱን አስገድዶ ሕገ ወጥ ተግባሩን ‹‹ሕጋዊ›› ለማድረግ ሞክሯል፡፡ በዚህም ቤተ ክርስቲያኒቱ ለዘመናት ያነበረችውን ቀኖና እና ሥርዓት አስቀምጣ ከመንግሥት ጋር አሳሪ ውል ለመግባት ተገድዳለች፡፡ በዚህ አሳሪ ስምምነት መሠረትም ቀደም ሲል በሕገ ወጥ መንገድ ተሹመው ከነበሩ ግለሰቦች መካከል የተወሰኑትን ‹‹ሕጋዊ›› አድርጋለች፡፡ በዚህም ምክንያት ሕገ ወጥነትን መለዮአቸው ያደረጉ አባቶች ቁጥር እምርታን እንዲያሳይ በሯን ከፍታለች፡፡
ባሳለፍነው ሐምሌ 9 ቀን 2015 ዓ.ም በቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ስለተከናወነው ሢመተ ኤጲስ ቆጶሳት በበርካታ የሃይማኖቱ ተከታዮች፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ ማኅበራት እና ሊቃውንት ሢመቱ እንዲዘገይ ልዩ ልዩ የተማጽኖ ደብዳቤዎች የጻፉ ቢኾንም፣ ጆሮ ዳባ ልበስ በመባላቸው እንደ ቀደመው ጊዜ በምዕመኑ ዘንድ ደስታ አልተፈጠረም፡፡ በሥነ ሥርዓቱ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ‹‹ዛሬ የተሾማችሁ ኤጲስ ቆጶሳት ቤተሰብን፣ ዘውግን፣ ብሔርን እና ዘመድ አዝማድን ብቻ ሳይሆን ራሳችሁንም ጭምር እንድትክዱ እናዝዛችኋለን ፤ አደራም እንላችኋለን›› የሚል ቤተ ክርስቲያኒቱ ያለችበትን ትልቅ አደጋ ያመላከተ መልዕክት ማስተላለፋቸው የሚነግረንም፣ ሢመቱ ምን ያህል በተረጋጋና ጊዜ በወሰደ ቀኖናዊ መመዘኛ የተከናወነ ሳይኾን የመንግሥትን ፍላጎት ለማስፈጸም ሲባል ብቻ በጥድፊያ የተደረገ መኾኑን ነው፡፡
ቤተ ክርስቲያኒቱ እየተጋፈጠችው ያለው አደጋ ግን እንዲህ በመንግሥት ፍላጎት እና በሐዋርያት ቀኖና መሃል ማመቻመቺያ በመፈለግ የሚረግብ አለመኾኑ በግልጽ መታመን ይገባዋል፡፡ የቤተ ክርስቲያኒቱ የሥርዓት መጻሕፍት የሚያዙትን ከመንፈሳዊ ሥልጣናቸው ተወግዘው የተነሱ ሰዎችን መልሶ በሊቀ ጳጳስ ማዕረግ የአዳዲስ ኤጲስ ቆጶሳት አስመራጭ በማድረግ የተፈጸመው ጥሰት ሳያንስ፣ ጵጵስና የጎሳ መልክ ተሰጥቶት ‹‹ንጹሕ ኦሮሞ ሾመንላችኋል›› እስከመባል የተደረሰበት ድፍረት በግልጽ የምናየውን ‹‹የትግራይ ቤተ ክህነት›› ከማዋለድ ጀምሮ ነገም መሰል አሳዛኝ ተግባር እንዲፈጸም አረንጓዴ መብራት አብርቷል፡፡
አሁንም ቢኾን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ራሷን በየጊዜው መንግሥት ከሚያዋልድላት አደጋዎች ተከላክላ ሕላዌዋን ለማስጠበቅ መከተል ያለባት የዕምነት አንቀጽዋን ብቻ ነው ብለን እናምናለን፡፡ በተለይም ገዢው የብልጽና መንግሥት ገና በመጀመሪያ ማኒፌስቶው ጥንታዊዎቹ ኦርቶዶክስ እና እስልምና ‹‹ለቁሳዊ ብልጽግና አይመቹም›› የሚል መርኅን ይዞ መነሳቱ ቤተ ክርስቲያኒቱን በዋዛ እንደማይተዋት ግልጽ ማሳያ ነበር፡፡ እናም ቤተ ክርስቲያን ዘመንን በመዋጀት እና መንግሥታቱን በመምሰል መሃል ያለውን ልዩነት ጠንቅቃ እስካልተራመደች ድረስ የከፉ አደጋዎች አሁንም በደጀ ሰላሟ አድፍጠዋል፡፡
