ኦነግ ዋና ቢሮው ከአራት ዓመታት በኋላ ተመለሰለት

Date:

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ከነሃሴ 2012 ዓ.ም ጀምሮ ተዘግቶ የነበረውን እና በአዲስ አበባ የሚገኘውን ዋና ቢሮው በይፋ እንደተመለሰለት የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ለሚ ገመቹ ለአዲስ ስታንዳርድ ገለጹ።

ጉዳዩን አስመልክቶ ከአዲስ ስታንዳርድ ጋር ቆይታ ያደረጉት የድርጅቱ ህዝብ ግንኙነት ሀላፊ አቶ ለሚ ገመቹ ከ2012 ዓ.ም መጨረሻ ነሃሴ ወር ጀምሮ ዋና ጽሕፈት ቤታቸውን ጨምሮ ሌሎች ቢሮዎች መዘጋታቸውን ገልጸው እንደ ድርጅት ጉዳዩን አስመልክቶ በተለያዩ መድረኮች ላይ ሲጠይቁ እንደነበረ አስረድተዋል።

“በይበልጥ የአዲስአበባ ከተማ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የቻለውን ያህል ጫና ሲያደርግ ነበረ” ያሉት አቶ ለሚ የምክር ቤቱ እንዲሁም ሌሎች ተወካዮች በተገኙበት ቢሯችን ለማስመለስ ችለናል ብለዋል።
አክለውም “ወደ ቢሯችን እንድንመለስ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የራሱን አስተዋጽኦ አድርጓል” ሲሉ አስታውቀዋል።

“ቢሮ መጠቀም ትልቁ ግባችን አይደለም። ግባችን ለሰፊው እና ለጭቁኑ ህዝብ ዓላማ ያለው ስራ መስራት ነው” ያሉት አቶ ለሚ ሆኖም ስራ ለመስራት ህዝባችንን ለማወያየት ሀሳብችንን ለመነጋገር እና ለመምከር ክፈተት ፈጥሮብን የነበረው አንዱ የዚሁ የቢሮ ጉዳይ ነው ብለዋል።

አያይዘውም ድርጅቱ ከ200 በላይ ጽህፈት ቤቶች እንዳሉት ጠቅሰው በቀጣይ በተዋረድ የተዘጉ ጽሕፈት ቤቶቻችን እንዲከፈቱልን ውትወታችን ይቀጥላል ብለዋል። ወደፊትም አደረጃጀቶቻችንን ለማጠናከር ተስፋ አድርገን እንሰራለን ሲሉ ተናግረዋል።

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ዛሬ ሰኔ 2 ቀን 2017 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ፣የዋና ቢሮው የማስመለስ ሂደቱ የተከናወነው የአዲስ አበባ ከተማ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አመራሮች በተገኙበት መሆኑን ገልጾ፣ “ይህን ለረጅም ጊዜ የዘለቀ ጥረት ማጠናቀቅ ወደፊት የተራመድንበት እርምጃ እንደሆነ እንመለከተዋለን” ብሏል።

ድርጅቱ ጽሕፈት ቤቱን ያጣው የአዲስ አበባ ፖሊስ ጽሕፈት ቤቱ ላይ ከበባ ካደረገ ከነሐሴ 2012 ዓ.ም ጀምሮ መሆኑ ይታወሳል።
በወቅቱ የፓርቲው ጊዜያዊ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ የነበሩት ባቴ ዑርጌሳ ለአዲስ ስታንዳርድ እንደተናገሩት፣ ፓርቲው በአዲስ አበባ የሚገኘው ዋና መስሪያ ቤቱ ነሐሴ 2012 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ ፖሊስ ከተያዘ ወዲህ ዋና መስሪያ ቤቱን ሳይገለገልበት ቆይቷል።

እንደ እርሳቸው ገለጻ፣ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ዋናው መሥሪያ ቤታቸው በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኃላፊነት ሥር መሆኑን እንደተነገራቸው አስታውቀዋል። “በዚያ ቀን ግቢው በፖሊስ ተይዞ ሊቀመንበሩ በኃይል እንዲወጡ ተደርገዋል” ብለዋል።

በወቅቱ የተሰጠን ሰበብ “ስማቸው ያልተጠቀሰ የፓርቲው አባላት ለደህንነት ሲሉ ዋና መሥሪያ ቤቱን ፖሊስ እንዲጠብቅላቸው ጠይቀዋል የሚል ነበር” ብለዋል። “ፖሊስ ግን እኛን ወደ ዋናው ጽሕፈት ቤት እንዳንገባ በመከልከል ለምን የጥበቃ አገልግሎት ለመስጠት እንደመረጠ አናውቅም” ሲሉ ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጸው ነበረ።

እስከ ነሃሴ ወር 2016 ዓ.ም ድረስ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር(ኦነግ) እና የኦሮሞ ፌደራሊሰት ኮንግረንስ ፓርቲ (ኦፌኮ)በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ ወደ 400 የሚጠጉ ቢሮዎቻቸው መዘጋታቸውን መግለጻቸውን በወቅቱ የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን መዘገባቸው ይታወሳል።

ገዢው ብልጽግና ፓርቲን ጨምሮ ከ50 በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በአባልነት የያዘው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በበኩሉ፤ ይህም በኦሮሚያ ክልል ሰላማዊ ትግል አንዲጠብ እና የትጥቅ ግጭት እንዲባባስ ምክንያት ሆኗል መባሉን በወቅቱ የተላለፈው የሸገር ሬድዮ ዘገባ ያሳያል።

የኦሮሞ ኮንግረንስ ፓርቲ አፌኮ የህዝብ ግኝኑነት ሃላፊ ሱልጣን ቃሲም ‘’ከ5 ዓመት በፊት የለውጡ ሰሞን መንግስትን ተማምነን ለሰላማዊ ትግል ምቹ ሁኔታ ይኖራል በሚል ተነሳሽነት 206 ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶችን ከፍተን ነበር አሁን 203 ተዘግተውብን የቀሩን ሶስት ጽህፈት ቤቶች ናቸው’’ ማለታቸውን ዘገባው አስደምጧል፡፡

ኦሮሞ ነጻነት ግንባር(ኦነግ) የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ለሚ ገመቹ በበኩላቸው ‘’በለውጡ ሰሞን በተስፋ ወደ ሁለት መቶ የሚጠጋ ቢሮዎች ከፍተን የነበረ ቢሆንም አሁን አንድም ቢሮ የለንም’’ ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የተፈናቀሉ ዜጎች በተጠለሉበት አካባቢ በቋሚነት መኖር የሚያስችላቸው 

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን የዳሰነች ወረዳ ከበኦሞ...

ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ 11ኛውን የኃይሌ ሆቴልና ሪዞርት በደብረ ብርሃን ከተማ አስመረቀ

ታዋቂው አትሌትና ባለሀብት ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ፣ በደብረ ብርሃን ከተማ...

በኢትዮጵያ ሪል ስቴት አልሚዎች ማህበር የተዘጋጀው የመጀመሪያው አህጉራዊ የሪል ስቴት ኤግዘቢሽን ተከፈተ

በኢትዮጵያ ሪል ስቴት አልሚዎች ማህበር አዘጋጅነት የመጀመሪያው አህጉራዊ የሪል...

በሊባኖስ እና በእሰራኤል የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት ተራዘመ

ትራምፕ በሊባኖስ እና በእሰራኤል መካከል የተደረሰው የተኩስ አቁም በሦስት...