ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ከትላንት ማክሰኞ ግንቦት 5፤ 2017 ዓ.ም ጀምሮ ከፖለቲካ ፓርቲነት መሰረዙን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ።
የምስረታውን የወርቅ ኢዮቤልዮ ባለፈው የካቲት ወር ያከበረው ህወሓት ከፓርቲነት የተሰረዘው፤ ቦርዱ ያዘዘውን “የእርምት እርምጃ” ተግባራዊ ባለማድረጉ መሆኑን ገልጿል።
ምርጫ ቦርድ ይህን ውሳኔ ያሳለፈው፤ ባለፈው የካቲት ወር መጀመሪያ ለፓርቲው የሰጠው ቀነ ገደብ በዛሬው ዕለት መጠናቀቁን ተከትሎ ነው። ቦርዱ ይህንን ቀነ ገደብ ባሳወቀበት መግለጫው፤ ህወሓት ጠቅላላ ጉባኤ ለማካሄድ የሚያስችል “የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን” በሶስት ወራት ውስጥ እንዲያካሄድ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር።
