የሕንዱ ‘ስካይሩት ኤሮስፔስ’ ኩባንያ በሀገሪቱ ታሪክ የመጀመሪያውን በግል የበለፀገ ‘ቪክራም-1’ የተሰኘ የምህዋር ሮኬት በ15 ደቂቃ ውስጥ የተሸከማቸውን ጭነቶች በ450 ኪሎ ሜትር ምህዋር ላይ በተሳካ ሁኔታ በማድረስ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ከፍቷል።
“የአጋማንተልእኮ” የተሰኘው ይህ ታሪካዊ በረራ፣ በዘመናዊ የ3D ህትመት ቴክኖሎጂ የተገነባ ሲሆን፥ ሕንድን በግል ድርጅት አማካኝነት ሮኬት የማስወንጨፍ አቅም ካገኙ የዓለማችን ጥቂት ሀገራት ተርታ እንድትሰለፍ አድርጓታል።
የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ይህ ስኬት የወጣቶችን ተሰጥኦና ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑን ገልጸው አበረታተዋል።
ይህ ስኬት ሕንድ የጠፈር ዘርፉን ለግል ኢንቨስትመንት ክፍት ማድረጓ ያስገኘው ትልቅ ውጤት ሲሆን፣ መንግሥት የሀገሪቱን የዓለም አቀፍ የጠፈር ኢኮኖሚ ድርሻ በአሁኑ ጊዜ ካለው 8 ቢሊዮን ዶላር በ2033 ወደ 44 ቢሊዮን ዶላር ለማሳደግ ላቀደው እቅድ ትልቅ መነሻ ሆኗል።
የ1 ቢሊዮን ዶላር ግምት ያለው ስካይሩት ኩባንያ ወደ መደበኛ የንግድ በረራዎች ለመሸጋገር የተዘጋጀ ሲሆን፣ ይህም ሕንድ በአነስተኛ ሳተላይት ማስወንጨፊያ ገበያ ውስጥ እንደ ስፔስኤክስ ካሉ ዓለም አቀፍ ግዙፍ ተቋማት ጋር ጠንካራ ተወዳዳሪ እንድትሆን ዕድል ይሰጣታል።
