የካቦድ ማርኬቲንግ ሶሉሽን እና የዶክሳ መሥራችና ሥራ አስኪያጅ ኤዶም ዳምጠው
‹‹አዲስ አበባ የአፍሪካ ኢንቨስትመንት መናኸሪያ እንድትኾን ነው የምናልመው››
በግዮን መጽሔት :- ንግዱ ዓለም ስኬት በአንድ ጀምበር የሚገኝ ድል ሳይሆን በጽናት፣ በእውቀትና በማያወለዳ ቆራጥነት የሚገነባ ረጅም መንገድ ነው፡፡ ዛሬ በመጽሔታችን እንግዳ አድርገን ያቀረብናት ግለሰብ ይህንኑ እውነት በሕይወት ተሞክሮዋ ያስመሰከረች ብርቱ ሴት ናት፡፡ በሪል ስቴት ማርኬቲንግና በሥልጠናው ዘርፍ አሻራዋን እያሳረፈች የምትገኘው የካቦድ ማርኬቲንግ ሶሉሽን እና የዶክሳ መሥራችና ሥራ አስኪያጅ — ኤዶም ዳምጠው፡፡
ግዮን:- በርካታ ወጣቶችን በሴልስና ማርኬቲንግ አሰልጣናችኋል። ለሰልጣኝ ወጣቶች መስፈርቱ ምን ነበር? ምን ያህል ወጣቶችስ አሰለጠናችሁ?
ኤዶም:- የመጀመሪያው ዙር ሥልጠና ሰኔ 2016 ዓ.ም ነበር፡፡ ሥልጠና የሰጠናቸዉ ልጆች ምን ያህል የአስተሳሰብ ለውጥ እንዳመጡ ሳይ እኮራለሁ፡፡በራሳቸው የተወሰኑ ድርጅቶች ላይ ሄደው ሲቀጠሩ ሳይም እጅግ እደሰታለሁ፡፡ እኛም ብንኾን በጣም በርካታ እስታፎችን ለራሳችን ወስደናል። ይህ በመኾኑም እጅግ ደስተኛ ነኝ። የሕይወቴ ስኬት ብዬ የማስበው ሰዎች ሲለወጡ ማየት ነው። እግዚአብሔር በእኔ ውስጥ ያስቀመጠው ዓላማ ሰዎችን ማንቃት ነው ብዬ አስባለሁ። አንዳንዴ ወጣትነት በራሱ ተግዳሮት አለው። ስለዚህ ወጣቶች ከዚያ ወጥተው የራሳቸው የሥራ ባህል እንዲኖራቸው ቢንቀሳቀሱ የሚል ሰፊ የኾነ እምነት አለኝ። ለዚያም ነው እንደዚህ ዐይነት ሥራ የምንሰራው፡፡
የሰልጣኞች አስተያየትም እጅግ በጣም ደስ የሚል ስለነበረ በሰራነው ሥራ እጅግ ኮርተናል። በዚህ በሁለተኛው ዙር ሥልጠና ከ600 በላይ ሠልጣኞች ነው ያሰለጠንነው፡፡ ሥልጠናውም የተሰጠው በዳግማዊ ምኒልክ ት/ቤት አዳራሽ፣ ከመጀመሪያው በተለየ መንገድ ለበርካታ ድርጅቶች ጎበዝ ሠልጣኞችን ቃለመጠይቅ ተደርገው እንዲቀጠሩ ጠይቀን አብዛኞቹ ተቀጥረዋል። በነገራችን ላይ እኔ በዚህ የስድስት ዓመት የሥራ ሕይወቴ ውስጥ የምቀጥራቸውን ሴልሶች ራሴ ኦሰልጥኜ ነው የምቀጥረው። በኛ ተቋም ውስጥ የምንቀጥራቸው ሰራተኞች አብዛኞቹን ማለትም ከ97% በላይ የሚኾኑትን አሰልጥነን ነው የምንቀጥረው። አሁን ላይ ሪል ስቴት ማርኬቱ ላይ የሚፈለገው ሰው ልምድ ያለው እና የሰለጠነ ሰው ነው። እንደኔ እምነት ግን ለወጣቶች እድል የሚሰጥ ነገር መኖር መቻል አለበት ብዬ አስባለሁ። ብዙ ቦታዎች ላይ የሥራ ልምድ የሌላቸውን ሰዎች አይቀጥሩም። የኛ ትልቁ ልዩነት ግን እዚህ ጋር ነው። ልምድ የሌላቸውን ሰዎች ቀጥረን እናሰለጥናቸዋለን።
በመጀመሪያውም ሆነ በሁለተኛው ዙር የሰጠነው ሥልጠና በነጻ ነው፡፡ ያሰለጠነው ደግሞ የትኛውም ዘርፍ ላይ ያለ የትኛውም ቦታ መሥራት የሚፈልግና ዲግሪም ኾነ ዲፕሎማ ሳይጠይቅ የትኛውም ቦታ ላይ ተቀጥሮ መስራት የሚፈልግ ወጣት ላይ ነው ትኩረት አድርገን ሥልጠናውን የሰጠነው።
ግዮን:- የእናንተ ተቋም በዋናነት የሚሰራው ምንድነው?
ኤዶም:- በዋናነት የማርኬቲንግ እና የሥልጠና ሥራዎችን እንሰራለን። የተለያዩ ድርጅቶችን ፕሮጀክቶች እናስተዋውቃለን እንሸጥላቸዋለን። የአሜሪካ ኢምባሲም ሄጄ እንዲሁ ሥልጠና ሰጥቻለው። ወደ ሪል ስቴት ገበያው ለመምጣት የሚፈልጉ ድርጅቶችንም እናማክራለን። ወደ ገበያው መግባት ለሚፈልጉ ማናቸውም አካላት የቢሮ መዋቅር ዘርግተን ሁሉንም ነገር አመቻችተን ወደ ሥራ እንዲገቡ የሙያ ድጋፍ እንሰጣለን፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ የኢቨንት ሥራዎችን በደንብ ነው የምንሰራው፡፡ ባለፈው ዓመት ሰኔ ላይም የመጀመሪያውን ኤክስፖ አድርገናል። እንዲህ ዐይነት ኤክስፖዎች ሲደረጉ ዋናው ጥቅም ራስን ማስተዋወቅና መሸጥ መቻል ነው። ያኔ ያዘጋጀነው ‹‹ካቦድ ኤክስፖ›› ብለን ነበር። ‹‹ቤት ለገዥው ሱቅ ለነጋዴው›› በሚል መሪ ቃል ነበር ኤክስፖን ያዘጋጀነው። በዚህም ከ15 በላይ ለሚኾኑ ድርጅቶች ሽያጭ አዘጋጀን። ለምሳሌ በወቅቱ ከእኛ ጋር ግንኙነት ከጀመሩ ድርጅቶች ውስጥ አንዱ ቴምር ሪል ስቴት ነው። ስፖንሰር አድርገውን ገቡ። ሥራውን የምንሰራው ግን እኛ ነበርን። እስካሁን ከነበረው ይሄ ልዩ የሚኾነው ወደኛ ጋር የሚመጡት ሴልሶቹ ነበሩ። ሲመጡ ካርድ ተልኮላቸው ነው የሚመጡት፤ የላካቸውን ነው የሚናገሩት፣ በዛ መሠረት ይስተናግዳሉ። በሶሻል ሚዲያ በኩል የሰራነው ሥራ አለ፣ እሱም በተገቢው መንገድ ተደራሽ አደረግን። የሚገርመው በዚህ ኤክስፖ ላይ በሦስት ቀን ውስጥ የተመዘገበው ሰው ከ2000 በላይ ነበር። ከዚያ ውስጥ ደግሞ ወደ ሰባ አንድ የሚኾኑ ሰዎች ለመግዛት ተዋውለው ነበር። በዚህ ላይ የተገኘውን ሁሉ አብዛኛውን ወደ ሽያጭ ቀይረነዋል። በአጠቃላይ ይሄኛው ኤክስፖ የተለመደ ዐይነት ኤክስፖ አልነበረም፡፡
ግዮን:- ካቦድ ካዘጋጀው ኤክስፖ ምን ተማረ? ለዚህ ዝግጅትስ የረዳው ነገር ምንድን ነው?
ኤዶም:- የእኛ ኤክስፖ ዝግጅት ካለቀ በኋላ የፓናል ውይይት አዘጋጅቼ ነበር። ምክንያቱም ገበያው ላይ ረጅም ጊዜ ስለቆየሁ ገቢ ከማግኘት በተጨማሪ የኾነ ነገር ማበርከት ፈለግኩኝ። ምክንያቱም በከተማዋ መነሳት ያለባቸው ጉዳዮች አሉ። ስለዚህ ለማውቃቸው ሰዎች ሐሳብ ስሰጥ ማኅበሩ ላይ ከሚሰሩ የቦርድ አባላት ጋር መገናኘት ቻልኩ። በዚህ ጊዜም ሐሳቡን ነገርኳቸው። ማኅበሩ ዋና የተቋቋመበት ሐሳብም እንዲህ ዐይነት ነገሮችን ለመስራት ነው። የገበያ ኹነቱ ላይ ለውጥ ለማምጣት ነው የተቋቋመው፡፡ በፊት ላይ የኛን ፕሮግራም የከፈቱልን ወይዘሮ ቅድስት ወልደ ጊዮርጊስ ነበሩ ፤ የቤቶች ኃላፊ፡፡ እዚህኛው የፓናል ውይይቱ ላይ ምክትላቸውን ላኩልን። ምክትሉ ክቡር አቶ በላይነህ በፕሮግራሙ ላይ ተገኙልን። እነዚህ ሰዎች በተገኙበት የሚገርም ፓናል ውይይት አደረግን። ስለዚህ የዛኛውን ውጤት ስላዩ ማኅበሩ በራሱ እንዲህ ዐይነት ነገሮችን እንዲያደርግ ጥቆማ ሰጠሁ። አንድ ጨረታ ነበር፣ ጨረታውን ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር በመጫረት አሸነፍን። ሥራውን በአራት ወራት ውስጥ ጀምረን በመሀል የሚስተካከሉ ነገሮች ስለነበሩ በቀጥታ ሥራውን የሰራነው ሁለት ወር ተኩል አካባቢ ነው። ድርጅታችን ካቦድም የማኅበሩ አባል ነው። የሪል ስቴት ማኅበሩ ሦስት ዲፓርትመንቶች አሉት። የኢንቨስትመንት ዲፓርት አለ፣ የማርኬቲንግ ዲፓርትመንት አለ፣ የንብረት ግምገማ ዲፓርትመንት አለ። ስለዚህ በማርኬቲንግ ዲፓርትመንቱ ላይ የእኛ ድርጅት ካቦድ አባል ኾኗል። በዚህም አባል በመኾናችን ማናቸውንም ሥራዎች ለመስራት አመቺ ኾኖልናል።

ግዮን:- በሀገራችን ውስጥ ከመቶ የሚበልጡ የሪል ስቴት ተቋማት አሉ። ኤክስፖ ላይ የተገኙት ወደ 28 የሚኾኑት ናቸው፤ ለምንድነው ቁጥራቸው በዚህ ልክ ያነሰው?
ኤዶም:- ሀገራችን ላይ በጣም በርካታ አልሚ ድርጅቶች ናቸው ያሉት። ወደ ከተማችን ስንመጣ ደግሞ የማኅበሩ አባል የኾኑት ወደ መቶ የሚጠጉ ይኖራሉ። አንዳንዶቹ አባል የኾኑት ማኅበሩ እንደተመሠረተ ነው። በነገራችን ላይ ማኅበሩ በጣም ትልልቅ ሥራዎችን ሠራ እንጂ ገና አጭር ጊዜው ነው። በዚ አጭር ጊዜ ውስጥ ከመንግሥት እና ከውጪ ተቋማት ጋር ብሎም ከመሰል የማኅበር ሰብስቦች ጋር ብዙ ሥራዎችን መስራት ችሏል። ስለኾነም በዚህ ዙሪያ የማኅበሩን ዓላማ ለማሳካት ገና ብዙ ሥራ ይጠብቀናል። ካሉት አባላት ውስጥ በመጀመሪያ ሁሉም ድርጅቶች ‹‹አክቲቭ ፕሮጀክት›› የላቸውም። ትልልቅ ድርጅቶች ኾነው ነገር ግን ፕሮጀክታቸውን ያልጨረሱ አሉ። ስለዚህ እነዛ ድርጅቶች ፕሮግራም ላይ ለመሳተፍ አያስችላቸውም። ፕሮጀክት ይዘው ነው መሳተፍ የሚችሉት። በዋናነት ተግዳሮት የነበረውም ለእኛ ይሄ ነው። በሌላ በኩል በርካታ አዳዲስ ድርጅቶች አሉ። ገና ሰፊ ሥራ ለመስራት እየተዘጋጁ ያሉ ናቸው።
በሌላ በኩል የማኅበሩን ዓላማና ዕቅድ ገና ያልተረዱ የተወሰኑ ድርጅቶችም አሉ። ስለዚህ እነሱ ላይ ደግሞ በቀጣይ በደንብ እንሰራለን። ሌላው ደግሞ ከግማሽ ዓመት በኋላ ነው ይሄን ነገር ያደረግነው። በዚህ ወቅት ብዙዎች ድርጅቶች በጀታቸውን ጨርሰው ነበር። እኛም ከዚህ ብዙ ነገር ተምረናል። ለሚቀጥለው ዓመት ከማኅበሩ ጋር አጋር ኾነን ይህን ሥራ የምንስራው እኛው ነን። ከቦርዶቹ ጀምሮ የተረዳነው ይህንን ነው። ስለዚህ ከአሁኑ ጀምሮ ጊዜያችንን ለማስተካከል እየሠራን ነዉ። ሌላው ደግሞ ሁለት ወር ተኩል አጭር ጊዜ ነው። እኛም መቶዎቹ እንዳሉ ይሳተፋሉ ብለን አላሰብንም ነበር። እስከ 45 የሚደርሱ ድርጅቶችን ብናስገባ ብለን አስበን ነበር። ከዛ ውስጥ ግን 28 የሚኾኑትን ማግኘት ችለናል። ይሄ እንደመጀመሪያ ዝግጅት በጣም ውጤታማ ዝግጅት ነው።
ግዮን:- ከውጭ የመጡ የሪል ስቴት ባለሙያዎች ተጋብዘዋል፤ በዚህ ዙሪያ ምን ያህል ተቋማት መጥተዋል? የነበረው የንግድ ልውውጥና የሙያ ትስስርስ እንዴት ነው?
ኤዶም:- በነገራችን ላይ የኢትዮጵያ ሪል ስቴት አልሚዎች ማኅበር እንዳለ ሁሉ የአፍሪካ ሪል ስቴት አልሚዎች ማኅበር የሚባል አለ፡፡ መቀመጫውን ያደረገው ናይጄሪያ ነው። የዚህ ድርጅት አብዛኞቹ አባላት ምሁራን ናቸው። የተወሰኑት ደግሞ በጣም ጥቂቶቹ አልሚዎች ናቸው። የሪል ስቴት ማኅበራችን ኢትዮጵያን የአፍሪካ ሪል ስቴት ማኅበር አባል አድርጓል፡፡ ይኽም ከሠራቸው አኩሪ ተግባራት አንዱ ነው፡፡ በመኾኑም ከኡጋንዳ፣ ናይጄሪያና ታንዛኒያ የመጡ ተሳታፊዎች ነበሩ። በቁጥር ደረጃ ወደ 12 ይኾናሉ። ከመንግሥት ባለስልጣናት የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር፣ ከፋይናንስ እና ከሌሎች ተቋማት ጋር በመኾን ለሁለት ቀናት በኢሊሊ ሆቴል ኮንፈረንስ ተከናውኗል። ይህን ፕሮግራም ተሳትፈዋል። በዚህም የአልሚዎቻችንን ሥራ አይተው ተደንቀዋል። እኛ ደግሞ አዲስ አበባ የአፍሪካ ኢንቨስትመንት መናኸሪያ እንድትኾን ነው የምናልመው። በቀጣዩ ጉባኤያችን ከብዙ የአፍሪካ ሀገራት የሚመጡ አልሚዎች ይኖራሉ፡፡ በተጨማሪም ከኤዥያ እና ከአውሮፓም ጭምር ይመጣሉ ብለን እናምናለን።
በዚህም የአዲስ አበባን አሁናዊ ገጽታና እድገት እንዲያዩ ስለፈለግን የኮሪደር ልማትና የወንዝ ዳር ደኖችን፣ የከተማዋን አጠቃላይ ኹኔታ አሳይተናቸው በጣም ተደንቀዋል። ባዩት ነገር ሁሉ በጣም ተደስተው ነበር። ማታ ላይ ደግሞ ዮድ አቢሲኒያ የእራት ግብዣ አድርገን ስጦታዎችን በተቋማችን ፕሬዚዳንት አቶ አለማየሁ በኩል አበርክተን ነው የሸኘናቸው። እነርሱም ኢንቨስትመንት እንደሚያደርጉ በኹነቱ በጣም እንደተደሰቱ ወደፊትም ብዙ ሥራዎችን አብረው እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል። ይኼ ደግሞ ሃገራችን የምትፈልገው ዋነኛው ነገር ነው፡፡
ግዮን:- በእናንተ ተቋም ውስጥ ችግሮች እና ተግዳሮት ቢያጋጥሙሽ በምን ዐይነት መልኩ ታልፉታላችሁ? ለዚህና ለሌሎች ጥያቄዎች ያቀረብነውን መልስ በሚቀጥሉት ቀናት ይዘን እንቀርባለን ።
ግዮን መጽሔት ቅጽ 8 ቁጥር 234 ግንቦት 2018 ዓ.ም
