የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከኔዘርላንድ የመድብለ ፓርቲ የዲሞክራሲ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ከተለያዩ የፓለቲካ ፓርቲዎች ለተውጣጡ ፓለቲከኞች በምርጫ ክርክር ክህሎት ላይ ስልጠና እየሰጠ ይገኛል።
የሥልጠናው ዋንኛ ዓላማ ፓለቲከኞች ለመራጩ የሚያቀርቡት ማኒፌስቶ (ፓሊሲዎችና ፕሮግራሞች) የህዝብ ቅቡልነት እንዲያገኙ የፓለቲከኞች የምርጫ ክርክር ክህሎትን ማሳደግ ላይ ያተኮረ ነው።
በምርጫ ክርክር አማካኝነት ተፎካካሪ የፓለቲካ ፓርቲዎች ለመራጩ ህዝብ በሚሰጡት አማራጭ የፓሊሲ አማራጮች ምክንያት መራጮች ዕውቀት ላይ ተመስርተው የሚበጃቸውን እንዲመርጡ ከማስቻሉ ባሻገር የዲሞክራሲ ተሳትፎ ባህልን ይጎለብታል።
በሥልጠና የመክፈቻ መርሃ ግብር ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሮ ሜላትወርቅ ኃይሉ 7ኛውን ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ ለማካሄድ አንድ ዓመት ገደማ ነው የቀረን። ስለሆነም ይህ ስልጠና የክርክር ክህሎታችሁን በማጎልበት የተደራጀ የፓለቲካ ፕሮግራሞቻችሁን፣ ፓሊሲዎቻችሁን ለመራጩ በማስተዋወቅ እና በማሳመን፤ መራጩ መረጃና ዕውቀት ላይ ተመስርቶ እንዲመርጥ ያስችለዋል ብለዋል።
