በሙትአንሳ ማር ቅዱስ ሚካኤል አንድነት ገዳም ግንባታዎች 65 በመቶ መጠናቀቃቸው ተገለፀ

Date:

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የማዕከላዊ ጎንደር ሀገረ ስብከት፣ የምስራቅ በለሳ ወረዳ ቤተክህነት ስር የሚገኘው የሙትአንሳ ማር ቅዱስ ሚካኤል አንድነት ገዳም፤ መንፈሳዊ አገልግሎቱን ከማጠናከር ጎን ለጎን የጀመራቸው ሁለንተናዊ የልማት ፕሮጀክቶች አፈጻጸም 65 በመቶ ደረጃ ላይ መድረሱን የገዳሙ አስተዳደር ባወጣው ወቅታዊ መግለጫ አስታውቋል።

በመግለጫው ገዳሙ ላለፉት ሁለት ዓመታት ከስድስት ወራት ጀምሮ ባከናወናቸው ዘለቄታዊ የልማት ሥራዎች፣ ማኅበራዊና መንፈሳዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት የሚያስችሉ በርካታ ስኬቶችን ማስመዝገቡ ተገልጿል።

ለረጅም ዘመናት ጠቦና የመፈራረስ አደጋ ተጋርጦበት የነበረውን ጥንታዊ የቅዱስ ሚካኤል ቤተ-መቅደስ በዘመናዊ መሐንዲሶች ዲዛይን መሠረት መልሶ የመገንባት ሥራ መጀመሩ ተገለፀ ።

በአሁኑ ወቅት ከ25 በመቶ በላይ ተከናውኗል ተብሏል ከገዳሙ እስከ በለሳ ከተማ የሚደርስ 8 ኪሎ ሜትር የኮረኮንች መንገድ፣ የንፁህ መጠጥ ውሃ ቁፋሮ፣ 179 ሜትር የገዳሙ ውስጣዊ የመንገድ ሥራ እና የኃይል አቅርቦት (መብራት) ዝርጋታዎች በመከናወን ላይ ይገኛሉ።

በተጨማሪም የወደፊቱን ትውልድ በሥነ-ምግባርና በእውቀት ለማነፅ ከቅድመ-አንደኛ ደረጃ እስከ 12ኛ ክፍል የሚያስተምር የአጠቃላይ ትምህርት ቤት ግንባታ እየተካሄደ ሲሆን፣ የሕንፃ ግንባታው 70 በመቶ ደርሷል ተብሏል::

ዘመናዊ የቅዱሳት መጻሕፍት ማተሚያ፣ የብረታ ብረትና የእንጨት ውጤቶች ማምረቻ እና የሕክምና ክሊኒክ ግንባታ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውም ተጠቁሟል::

በማኅበራዊ ሚዲያና በተለያዩ የሕዝብ ግንኙነት ሥራዎች አማካኝነት እስካሁን ድረስ 52,ሚሊዮን 6 መቶ 40 ሺህ ብር የቃል ኪዳን ድጋፍ የተሰበሰበ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 11 ሚሊዮን 3 መቶ 20 ሺህ ብር በጥሬ ገንዘብ ገቢ ሆኖ ለልማት ሥራዎች እንደዋለ ተገልጿል።

ገዳሙ ባስመዘገባቸው የእድገት ተስፋዎች መካከል በርካታ ተግዳሮቶች እንደገጠሙት በተለይም የሕንፃ መገንቢያ ቁሳቁሶች ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ መጨመር፣ በገበያ ላይ የዕቃዎች እጥረት መከሰት፣ እንዲሁም በማኅበራዊ ሚዲያ (በተለይም በቲክቶክ) ላይ አንዳንድ አካላት ትክክለኛ ያልሆነና የገዳሙን መልካም ስም የሚያጠለሽ መረጃ ማሰራጨታቸው ከባድ ፈተና ሆኖ እንደቆየ ተነስቷል።

እነዚህን ዘለቄታዊ የልማት ፕሮጀክቶች በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ውስጥ ሙሉ በሙሉ አጠናቆ ለማስረከብና ገዳሙን ሙሉ በሙሉ ራሱን የቻለ የልማት ማዕከል ለማድረግ በአጠቃላይ 210,000,000 (ሁለት መቶ አሥር ሚሊዮን ) ብር እንደሚያስፈልግ ተገልጿል።

አስተዳደሩ በመግለጫው ማጠቃለያ ላይ፤ ሙሉ በሙሉ ግልፅነት ባለውና በሕጋዊ የባንክ አካውንት ብቻ በሚከናወን አሠራር ገዳሙን እየደገፉ ላሉ ምዕመናን፣ የሀገረ ስብከት መሪዎችና የመንግሥት አካላት የላቀ ምስጋና ያቀረበ ሲሆን፣ የተጀመሩት ታላላቅ የልማት ሥራዎች ዳር እንዲደርሱ መላው የክርስቲያን ማኅበረሰብ በጸሎት፣ በእውቀትና በፋይናንስ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርቧል

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ ከፖለቲካ ራሳቸውን አገለሉ

ላለፉት 5 አስቸጋሪና ፈታኝ ዓመታት (ከ2014 እስከ 2018 ዓ.ም)...

ንባብ ለሕይወት  እየመጣ ነው !!!

በንባብ ለሕይወት ፕሮጀክትና በኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት አዘጋጅነት የሚካሄደው...

“ወጣቱን በጉልበት እያፈሱ ወደ ጦርነት እየነዱት ነው!”

"ሰላም፣ ዴሞክራሲና ልማት በትግራይ፦ የመገናኛ ብዙኃን እና የማኅበረሰብ አንቂዎች...