በከባድ መሣሪያ ተኩስ ልውውጥ ሳይቀር የታጀበው በሞያሌ የተቀሰቀሰው ግጭት ወደ ሶስት ተጨማሪ ወረዳዎች ተስፋፋበኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን በምትገኘው የድንበር ከተማ ሞያሌ፣ የሶማሌ ክልል ሰንደቅ ዓላማ በመሰቀሉ ሳቢያ በተፈጠረ ውዝግብ እና ጥቅምት 8 ቀን 2017 ዓ.ም. የአንድ የ13 ዓመት ታዳጊ ልጃገረድ ህይወት ማለፉን ተከተሎ የተቀሰቀሰው ግጭት ተባብሶ የቀጠለ ሲሆን፣ በኦሮሚያ እና በሶማሌ ክልል የጸጥታ ኃይሎች መካከል የከባድ መሣሪያ ተኩስ ልውውጥ ተካሂዷል።
ከረቡዕ ምሽት ጀምሮ ሲጋጋል የቆየው ውጥረት ሐሙስ ዕለት ወደ የለየለት ግጭት የተቀየረ ሲሆን፣ በደቡብ ኦሮሚያ በሚገኙ ጉሚ ኤልዳሎ፣ ዋጪሌ እና አሬሮ ወረዳዎች ውስጥ በሚገኙ አንዳንድ አካባቢዎች ጭምር መስፋፋቱንነዋሪዎች እና የአካባቢው የጸጥታ ኃላፊዎች ገልጸዋል።
የሞያሌ ከተማ ነዋሪዎች እንደተናገሩት ግጭቱ ሐሙስ ዕለት ከማለዳው 11:30 ገደማ በነማለብ፣ ጫሙቅ፣ ቦሌ፣ ቀበሌ 01 እና ዋቆ ዶጎ በተባሉ በርካታ አካባቢዎች ተቀስቅሷል።
የደቡብ ኦሮሚያ የጸጥታ ኃላፊዎች ግጭቱ በኋላ ላይ ወደ ምስራቅ ቦረና ዞን አካባቢዎች መስፋፋቱን አረጋግጠዋል፤ ይህም በጉሚ ኤልዳሎ ወረዳ የሚገኘውን መልካ ጉባ ቀበሌ፣ በዋጪሌ ወረዳ የሚገኙትን መልካ አዲ እና መልካ ጮፊ ቀበሌዎችን፣ እንዲሁም በአሬሮ ወረዳ “ኤላ ኦርቢ” በመባል የሚታወቀውን አካባቢ ሳይቀር ተዛምቷል።
የሞያሌ ነዋሪ የሆኑት አቶ ዋቆ ሁሴን እንደገለጹት፣ የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል ሰንደቅ ዓላማ ለመስቀል ያደረገው ሙከራ፣ የ13 ዓመቷ ዲቆ ጃታን አጋ መገደል እና ማክሰኞ ምሽት በአንድ የከተማዋ ኃላፊ ላይ “የግድያ ሙከራ ሊፈጸም ነው” በሚል የተሰራጨ ያልተረጋገጠ አሉባልታ ለግጭቱ መባባስ ምክንያት ከሆኑት መካከል ይጠቀሳሉ ብለዋል።
በሐሙስ ዕለቱ ግጭት ዙሪያ አቶ ዋቆ ሲናገሩ “ራሳችንን ለመከላከል እና ለመጠበቅ እርምጃ ወስደናል” ሲሉም ተናግረዋል።በኦሮሚያ ወገን ያሉ የሞያሌ ከተማ አንድ የመንግስት ኃላፊ በበኩላቸው ግጭቱ በማለዳ በበርካታ ቦታዎች የተቀሰቀሰ መሆኑን ገልጸው፣ “በቅርቡ የተለያዩ ትንኮሳዎችን ሲፈጽሙ በቆዩ ኃይሎች በማለዳ በሕዝባችን ላይ የታወጀ ጦርነት ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
ይሁንና ከቤተሰቦቻቸው ጋር ሸሽተው ወደ ኬንያ ሞያሌ እሉ አካባቢ የተሰደዱ አንድ የሶማሌ ብሔር ተወላጅ የከተማዋ ነዋሪ በኦሮሚያው ኃላፊ ወገን የቀረበውን ክስ ውድቅ ያደረጉ ቢሆንም፣ የሰንደቅ ዓላማ ውዝግቡ የግጭቱ ዋነኛ መንስኤ መሆኑን አረጋግጠዋል።
“ጥቅምት 12 ቀን ጠዋት ተኩስ የከፈቱብን የቦረና ወገን ኃይሎች ናቸው፤ ሰንደቅ ዓላማችንንም እንዳንሰቅል ከልክለውናል” ብለዋል። አክለውም ግጭቱ ከተቀሰቀሰ በኋላ የቦረና ወገን ኃይሎች የሶማሌ (የጋሬ ማህበረሰብ) ነዋሪዎች የሆኑ ግለሰቦች መኖሪያ ቤቶችን፣ መሥሪያ ቤቶችን እና የተለያዩ የማስታወቂያ ሰሌዳዎችን ማቃጠላቸውን ገልጸዋል።
በጫሙቅ አካባቢ የሚኖሩ ሌላ የሞያሌ ነዋሪ ደግሞ መንግሥት የሚደግፋቸው እና በከባድ መሣሪያ የተደራጁ የሶማሌ ክልል ኃይሎች ጥቃት እንዳደረሱባቸው ተናግረዋል።
ነዋሪው አክለውም ከተገደሉ ታጣቂዎች በተገኙ መታወቂያዎች እና የጦር መገናኛ መሣሪያዎች አማካኝነት ጥቃት አድራሾቹን መለየት መቻሉን ገልጸዋል።
የሁለቱም ወገኖች የጸጥታ ኃላፊዎች በግጭቱ ምክንያት የሰው ህይወት ማለፉን እና አካል ጉዳት መድረሱን አረጋግጠዋል። ነገር ግን ሁለቱም ወገኖች “በሌላው ወገን ትንኮሳ ተፈጽሞብኛል” ቢሉም፣ “ወታደራዊ ምስጢርን” ለመጠበቅ በሚል የሞቱትን እና የቆሰሉትን ሰዎች ትክክለኛ ቁጥር ከመግለጽ ተቆጥበዋል።
ከማለዳው 11:30 ገደማ የጀመረው ግጭት በምሳ ሰዓት አካባቢ ረገብ ያለ ቢመስልም፣ ይህ ዘገባ እስከ ተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ቀጥሎ እንደነበር የሁለቱም ወገን ነዋሪዎች ገልጸዋል።ግጭቱ ወደ ሌሎች ወረዳዎች ተስፋፍቷልከሰዓት በኋላ ግጭቱ ወደ ምስራቅ ቦረና ዞን መስፋፋቱንና በጉሚ ኤልዳሎ ወረዳ በሚገኘው መልካ ጉባ ቀበሌ፣ በዋጪሌ ወረዳ በሚገኙት መልካ አዲ እና መልካ ጮፊ ቀበሌዎች፣ እንዲሁም በአሬሮ ወረዳ ኤላ ኦርቢ አካባቢ ተጠናክሮ መቀጠሉን ነዋሪዎች እና ኃላፊዎች አረጋግጠዋል።
በግጭቱ ምክንያት በሞያሌ ከተማ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ ቆሟል። በርካታ በግጭቱ ያልተሳተፉ ንጹሃን፣ በተለይም ሴቶች እና ሕፃናት ከከተማዋ የሸሹ ሲሆን፣ በሁለቱም ወገን ያሉ የዓይን ምስክሮች እና ነዋሪዎች በርካታ ቤቶች ስለ መቃጠላቸው ምስክርነት ሰጥተዋል።
አስተያየታቸውን የሰጡ የዓይን ምስክሮች ይህ ዘገባ እስከ ተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ወይም የፌዴራል ፖሊስ በግጭቱ ውስጥ ጣልቃ አለመግባታቸውን ተናግረዋል።
የግጭቱ መነሻየታዳጊዋ መገደል ተቃውሞዎችን፣ የንግድ ድርጅቶች መዘጋትን እና የትራንስፖርት አገልግሎት መቋረጥን ያስከተለ ሲሆን፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና የጸጥታ ኃላፊዎች ሰንደቅ ዓላማውን ለማንሳት ተወያይው ውሳኔ አሳልፈዋል። ነገር ግን ከማክሰኞ ጀምሮ ውዝግቡ ሳይበርድ ይልቁንም ወደ ሰፊ ግጭት ያደገ ሲሆን፣ ነዋሪዎች የሰው ህይወት ማለፉን፣ የንብረት ውድመትን እና የንጹሃን መፈናቀልን ማስከተሉን እማኝነት ሰጥተዋል።
በኦሮሚያ እና በሶማሌ ክልሎች በጋራ የምትተዳደረውና የሁለቱ ክልሎች አስተዳደሮች በይዞታቸው በአንዳንድ ቦታዎች በአንድ መንገድ ብቻ በሚለያዩባት የሞያሌ ከተማ፣ በኦሮሚያ ቦረና እና በሶማሌ ክልል ጋሬ ማህበረሰቦች መካከል ከአወዛጋቢ የድንበር ይዞታዎች ጋር በተያያዘ ተደጋጋሚ ውጥረት እና አልፎ አልፎም ግጭቶች የምታስተደናግድ ከተማ ናት።
ግጭቶቱም ብዙውን ጊዜ ለሰው ህይወት ማለፍ፣ ለመፈናቀል እና የነዋሪዎች ቤቶች ለመቃጠል ምክንያት በመሆን ቀጥለዋል።በሐምሌ እና ነሐሴ 2017 ዓ.ም. የሶማሌ ክልላዊ መንግሥት አዳዲስ ወረዳዎችን እና የዞን አስተዳደሮችን የሚያቋቁም የአስተዳደር መዋቅር የመለወጥ ዕቅድ ካጸደቀ በኋላ ግጭት ተከስቶ እንደነበር መዘገባችን እይዘነጋም።
እርምጃው አወዛጋቢ በሆኑ ቦታዎች ላይ በሚያመጣው ለውጥ ምክንያት ከኦሮሞ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ተቃውሞም አስተናግዶ ነበር። በዚሁ ወቅትም በግጭቶቹ ወደ ሁለቱም ክልሎች በርካታ የድንበር አካባቢዎች ተዛምተው የበርካታ ንጹሃንን ህይወት ከመቅሰፋቸውም በላይ ከ288,000 በላይ ሰዎችንከቄያቸው እንዲፈናቀሉ ምክንያት ሆነዋል።
አዲስ ስታንዳርድ
