በ2017 በጀት ዓመት በቆዳና ቆዳ ውጤቶች ዘርፍ 217 ሚሊዮን ዶላር ተኪ ምርት መመረቱን የቆዳ ኢንዱስትሪ ምርምርና ልማት ማዕከል አስታወቀ።
የማዕከሉ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዙልፍካር አባጅሐድ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ በ2017 በጀት ዓመት 217 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ የቆዳ ውጤቶች እና ለኢንዱስትሪዎች ግብዓት የሚውሉ ተኪ ምርቶች ተመርተዋል።
የዘርፉን ምርትና ምርታማነት በማሳደግ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ገበያዎችን በአግባቡ በመጠቀም ለሀገር ኢኮኖሚ እድገት ያለውን ሚና ለማሳደግ እየተሠራ ነው ብለዋል።
ለገበያ የሚቀርቡ ምርቶች ዓይነትና ጥራት እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ የሀገር ውስጥ ምርትን የመጠቀም ባሕል እያደገ መጥቷል ብለዋል።
አብነትም የጸጥታ አካላትን ጫማ ፍላጎት ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ ምርቶች መተካት እንደተቻለ ገልጸዋል።
ኢንዱስትሪዎች በዓለም አቀፍ ገበያዎች መግባት የሚችሉበትን መስፈርት እንዲያሟሉ እየተሠራ መሆኑን አንስተው፤ እስካሁንም ሰባት ፋብሪካዎች ተገቢውን መስፈርት አሟልተው ዓለም አቀፍ ምስክር ወረቀት ማግኘት መቻላቸውን ገልጸዋል።
ከማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙ ኢንዱስትሪዎች የሚፈልጉትን የውጭ ምንዛሪ ማግኘት የሚችሉበት ሁኔታ መፈጠሩንና ለዘርፉ መነቃቃት ተጨማሪ አቅም መፍጠሩንም አብራርተዋል።
በ2017 በጀት ዓመት ከቆዳና ቆዳ ውጤቶች 25 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ተገኝቷ ያሉት ሥራ አስኪያጁ፤ በ2018 በጀት ዓመትም የውጭ ምንዛሪ ግኝቱን ወደ 50 ሚሊዮን ዶላር ለማሳደግ መታቀዱን ገልጸዋል።
