ሴት ተማሪዎች የወር አበባ ሲያጋጥማቸው ከትምህርት ቤት የመቅረት እና ከህብረተሰቡ የመገለል ሁኔታዎች አሁንም ድረስ እንደሚስተዋል ይነገራል፡፡
ይህንን ችግር ለመፍታት በትምህርት ሚኒስቴር በኩል የተጀመሩ ስራዎች መኖራቸውን የገለፁት በትምህርት ሚኒስቴር የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳዮች አካቶ ትግበራ ስራ አስፈፃሚ ምህረተክርስቶስ ታምሩ ናቸው፡፡
ሴት ተማሪዎች በወር አበባ ወቅት ትኩረት አድርገው ትምህርታቸውን መከታተል እንደማይችሉ እና የግንዛቤ ክፍተት በመኖሩም መገለል እንደሚደርስባቸው በመጥቀስ ይህንን ለመፍታት ነባር ትምህርት ቤቶች ባላቸው ቦታ የንፅህና መጠበቂያ መቀየሪያ እና ማረፊያ ክፍል እንዲያዘጋጁ እየተደረገ መሆኑ ገልፀዋል፡፡
እንዲሁም አዳዲስ ይገነባሉ ተብሎ በተዘጋጁ የትምህርት ቤት ፕላን ውስጥም ለሴቶች ለብቻ የሚገነቡ ክፍሎች መኖራቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ለተማሪዎች ምቹ የሆነ አካባቢን እና የንፅህና መጠበቂያን ማቅረብ 36 ፐርሰንት የትምህርት ክትትልን የሚጨምር በመሆኑ ትምህርት ሚኒስቴር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
አሁንም ድረስ በገጠሪቱ የሀገሪቱ ክፍልም ሆነ በከተሞች በወር አበባ ምክንያት ከትምህርት ገበታቸው እስከ አራት ቀን የሚቀሩ ሰቶች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
