በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ዛሬ እየተሽከረከረ ያለ ልብ የሚሰብር የሁለት መንትዮች ሞት ዜና አለ። የለጋዎቹ እህትማማቾች የእኑዬ እና የቡዬ ሞት።
በደቡቡ የሀገራችን ክፍል፣ በአረንጓዴውና ለምለሙ የአለታ ጩኮ ምድር ሳምራዊት (እኑዬ) እና ሰላማዊት (ቡዬ) ሲወለዱ ምድር “ሁለት ሆኑ” አላለችም፤ ይልቁንም “አንድ ነፍስ በሁለት አካል ተከፈለች” እንጂ።
እኑዬና ቡዬ መለያየት የማይችሉ፣ እንደ ጥላና አካል የተጣበቁ፣ የሳቅ ምንጫቸውም ሆነ የለቅሶ ዜማቸው አንድ የነበረ መንትዮች ነበሩ። ዛሬ ግን የአለታ ጩኮ ፀሐይ የጠለቀች ይመስላል፤ ወፎች ዝማሬያቸውን አቁመዋል፤ የሲዳማ ምድርም በከባድ ሐዘን ተውጣለች።
በሀዋሳ ፋርማ ኮሌጅ የነበራቸው ቆይታ የዕውቀት ብቻ ሳይሆን የትጋትም ነበር። አባታቸው፣ ያ ደግ አባት፣ በየሳምንቱ ከአለታ ጩኮ ሀዋሳ ድረስ 65 ኪሎ ሜትር እየተመላለሰ ልጆቹን ሲጠይቅ፣ በዓይኖቹ ውስጥ የሚታየው ብርሃን የራሱ ሳይሆን የልጆቹ ተስፋ ነበር።
“አባዬ መጣ!” ሲሉ አቅፈውት፣ እርሱም “የነገዎቹ የህክምና ባለሙያዎች ” እያለ ግንባራቸውን ሲስማቸው፣ ያ ምስል በገነት ውስጥ ያለ ድባብ ይመስል ነበር። አባትየው በልጆቹ ይኮራ ነበር።በስነ-ምግባራቸው፣ ትምህርት ጥንካሬያቸው እና በአንድነታቸው ያስቀና ነበር።
በሌላ በኩል፣ እናታቸው በሩቅ ሀገር በጣሊያን ሆና ቀንና ሌሊት ትለፋ ነበር። የምትለፋው ለራሷ አልነበረም፤ “ልጆቼን አጠገቤ ባደረኳቸው፣ የተሻለ ዓለም ባሳየኋቸው” በሚል የእናትነት ናፍቆት እንጂ።
ከእናታቸው ጋር በየቀኑ በቪዲዮ ኮል ሲያወሩ፣ በስክሪኑ ላይ የሚታየው የእኑዬና የቡዬ ፈገግታ ለእናቲቱ የሕይወት ስንቅ ነበር። “ቅርብ ቀን እንገናኛለን እማዬ” የሚለው ቃል የሁለቱም ወገን ዜማ ነበር።
የጉዞ ሰነዶቻቸው አያዘጋጁ ፣ ቦርሳዎቻቸው እየሸከፉ ፣ ህልማቸውም ክንፍ አውጥቶ ለመብረር ዝግጁ ነበር። ጣሊያን ሀገር ያለው ቤታቸው በናፍቆት ይጠብቃቸው ነበር፤ ግን ታሪኩ ሌላ ሆነ።
ያ የጨለማ ቀን፦ ህልም የተቀጠፈበት ሰዓት
ያ አስከፊ ቀን ግን በታሪክ ማህደር ውስጥ በጥቁር ቀለም ተከተበ። ከሀዋሳ ተነስተው ወደ አዲስ አበባ፣ የጉዟቸውን የመጨረሻ ምዕራፍ ለመጨረስ ሲጓዙ፣ መንገዱ ግን ወደ ሌላ ዓለም ወሰዳቸው። ሻሸመኔን አልፈው ወደ ኩየራ ሲቃረቡ፣ ያ ተላላኪ መኪና የፊት ጎማውን አጣ።
መኪናው ሲገለበጥ፣ ያ ሁሉ ሳቅ፣ ያ ሁሉ የጣሊያን ናፍቆት፣ ያ ሁሉ የአባት ምርቃት በቅጽበት በደመና ተሸፈነ።
ሳምራዊት (እኑዬ) ገና በአደጋው ስፍራ ነፍሷን ለፈጣሪ ሰጠች። ያ ውብ ፊቷ በደም ተሸፈነ፤ ያ ተስፋ የሰነቀው ልቧ መምታቱን አቆመ። መንትያዋ ሰላማዊት (ቡዬ) ግን፣ ግማሽ አካሏንና ግማሽ ነፍሷን በዚያው መንገድ ላይ ጥላ፣ በከባድ ቆሰለች። ወደ አዲስ አበባ ለህክምና ተወሰደች። ነገር ግን ደራሲያን እንደሚሉት “መንትዮች የሕይወት ገመዳቸው የተቆላለፈ ነው፤ አንዱ ሲበጠስ ሌላው መቆም አይችልም”።
ይህ በአለታ ጩኮ የተከሰተው መሪር ሐዘን፣ ከዓመታት በፊት በሩቅዋ ሜክሲኮ የተከሰተ ሌላ ዘግናኝ ታሪክን ያስታውሰናል። ማሪያና እና ሉቺያ የተባሉ መንትዮች ልክ እንደ እኑዬ እና ቡዬ ሁሉ፣ ሕይወታቸው በአንድ ክር የተቋጠረ ነበር። የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን አጠናቅቀው ለተሻለ ሥራ ወደ ዋና ከተማው በሚጓዙበት ወቅት፣ በመኪናቸው ላይ በደረሰ የጎማ መፈንዳት አደጋ ሕይወታቸው አጣጥፎታል።
የሚያስለቅሰው ግን የሞታቸው ሁኔታ ነበር፤ ማሪያና በቦታው ስትሞት፣ ሉቺያ ሆስፒታል ገብታ ለሰባት ቀናት በስቃይ ቆይታለች። በሰባተኛው ቀን ግን፣ ሉቺያ ምንም እንኳ የእህቷን መሞት ማንም ባይነግራትም፣ በድንገት ከተኛችበት ብንን ብላ “ማሪያና እየጠራችኝ ነው፣ ልሂድላት” በማለት የመጨረሻ ትንፋሿን አውጥታለች።
ዛሬ በአለታ ጩኮ ምድር የደገመው ይህ ታሪክ ነው! እኑዬ ቀድማ ስታልፍ ከአራት ቀን በኋላ ትናንት ማታ ቡዬም በሆስፒታል አልጋ ላይ ሆና የነፍሷን ግማሽ መሄድ ሳታውቅ አልቀረችም። የአራት ቀን ልዩነት! ያ አራት ቀን ስቃይ ለቡዬ ሳይሆን ለሚመለከቷት ወላጆች ሲኦል ነበር።
መንትዮች ሲለያዩ እንዲህ ነው፤ አንደኛው ሲሄድ ሌላኛው በምድር ላይ የሚያቆየው አንዳችም ትርጉም አይኖረውም። ቡዬ እህቷ የሌለችበትን ጣሊያን፣ እህቷ የሌለችበትን አለታ ጩኮ አልፈለገችውም። ይልቁንም ያንን የሰማይ መንገድ መርጣ እጇን ዘርግታ ተከተለቻት።
ይህ የአጋጣሚ ስብስብ ሳይሆን፣ የሁለት ነፍሶች ዘላለማዊ ቃልኪዳን ነው።
በአንድ ማህፀን ተፈጥረው፣ በአንድ አልጋ ተኝተው፣ በአንድ ሳህን በልተው፣ በአንድ መኪና ተሳፍረው፣ በመጨረሻም በአንድ መቃብር ለማረፍ መወሰናቸው የሰው ልጅን ደካማነትና የፈጣሪን ምስጢራዊ አሠራር ያሳያል።
ያ በየሳምንቱ የሚመላለሰው አባት፣ አሁን የሚመላለስበት ምክንያት የለውም። እጆቹ ባዶ ቀርተዋል። “ልጆቼን ላስተምር” ብሎ የለፋው አባት፣ ዛሬ በልጆቹ መቃብር ላይ መቆሙን የትኛው ቃል ሊገልጸው ይችላል? ልጆቹን ለጣሊያን ጉዞ እያመቻቸ ለሞት መቀበል ምንኛ ከባድ ነው!
ጣሊያን ሀገር ሆና የልጆቿን መምጣት ስትጠባበቅ የነበረች እናት፣ አሁን የምትጠብቀው ልጆቿን ሳይሆን የልጆቿን አስከሬን ሆነ። “ቪዛው ይሳካል ” ብላ ተስፋ የነበራት እናት፣ ዛሬ ያ ቪዛ ወደማይመለሱበት ሀገር መሸኛ መሆኑን ስታውቅ የምትሰማው ስቃይ በምድራዊ ቃላት አይለካም። በቪዲዮ ኮል የታዩት ፊቶች ዛሬ በአፈር ተሸፍነዋል።
የእኑዬ እና የቡዬ ህልም የተቀጨው በክፉው የመኪና አደጋ ነው። ዛሬ በሀገራችን ጎዳናዎች ላይ የሚፈሰው ደም ከጦር ሜዳ የከፋ ሆኗል። የመኪና አደጋ ስጋና ደም ብቻ ሳይሆን፣ ተስፋን የሚቀጥፍ፣ ቤተሰብን የሚበትን፣ ሀገርን ዕንቁ የሚያሳጣ ጨካኝ ገዳይ ነው።
እንደ እኑዬ እና ቡዬ ያሉ የነገ የሀገር ተስፋዎች፣ በቴክኒክ ብልሽት ወይም በቸልተኝነት ምክንያት በሚከሰቱ አደጋዎች እንደ ቅጠል ሲረግፉ ማየት የልብ ስብራት ነው። አንድ የላላ ብሎን፣ አንድ የተላላጠ ጎማ ወይም የአፍታ መዘናጋት የዓመታት ድካምን ከንቱ ያደርጋል።
ይህ አደጋ ወላጆችን ያለ ደጋፊ፣ እናቶችን ያለ ሳቅ፣ ሀገርን ያለ ምሁር ያስቀራል።
ዛሬ አለታ ጩኮ ዝም ብላለች። የሁለቱ ኮረዳዎች ሳቅ በከተማዋ ጎዳናዎች ላይ አይሰማም። የሲዳማ ምድር “ሁለት ዕንቁዎቼን አጣሁ” ብላ አዝናለች። እንደ እኑዬና እንደ ቡዬ ያሉ ቅን፣ ትጉህና ተስፈኛ ወጣቶች በአጭር ሲቀሩ፣ ሀገር ታለቅሳለች!!!
ከፊደል ፖስት
