የአይን ብሌን ከበጎ ፈቃደኞች በመሰብሰብ እይታቸውን ላጡ ዜጎች ሕክምና በመስጠት ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ደምና ህብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት፤ በሀገሪቱ ሁለተኛው የአይን ባንክ በጥቂት ቀናት ውስጥ ሥራ ይጀምራል ሲል አስታውቋል፡፡
ከ22 ዓመታት በፊት በአዲስ አበባ ሚኒሊክ ሆስፒታል ውስጥ ሥራ በጀመረው የአይን ባንክ ብቻ ሲገለገል የቆየው ተቋሙ፤ በጥቂት ቀናት ውስጥ ሁለተኛውን የአይን ባንክ ሥራ እንደሚያስጀምር የኢትዮጵያ ደምና ህብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አሸናፊ ታዘበው ተናግረዋል፡፡
በሀገሪቱ ሁለተኛው የአይን ባንክ በጅማ ከተማ የሚከፈት ሲሆን፤ ይህም የኢትዮጵያ ደምና ህብረ ህዋስ ባንከ አገልግሎት ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ጋር በመነጋገር እየተዘጋጀ ነው ሲሉ ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡
የአይን ባንክ ማቋቋም ከፍተኛ ሤራን የሚጠይቅ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፤ በጅማ ከተማ በቅርቡ ወደሤራ የሚገባውን ማዕከል ለመክፈት የዝግጅት ሥራው ባለፈው ዓመት እንደተጀመረ ጠቁመዋል፡፡
“በአሁኑ ወቅት ይኸው ሥራ ተጠናቋል ማለት ይቻላል ያሉም ሲሆን፤ በሁለትና ሦስት ቀናት ውስጥም የአይን ባንኩ የመጀመሪያውን የአይን ብሌን ንቀለ ተከተላ በማድረግ የአይን ብርሃን መመለስ እንደሚጀምር ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም የተያዘው የሕዳር ወር ‘የአይን ብሌን ልገሳ ወር’ በሚል ለሁለተኛ ጊዜ እየተከበረ መሆኑን ተከትሎ፤ የአይን ባንኩን በዚሁ ወር በይፋ እናስመርቃለን ሲሉ ተናግረዋል፡፡
እስካሁን በኢትዮጵያ አንድ የአይን ባንክ በአዲስ አበባ ብቻ እንደሚገኝ የገለጹ ሲሆን፤ በመዲናዋ በስምንት ሆስፒታሎች ላይ ደግሞ የአይን ብሌን ይሰበሰባል ብለዋል፡፡
የአይን ብሌን ጠባሳ ያለባቸውን ወገኖች ለማከም የአይን ባንኮችን በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ለመክፈት እቅድ መያዙንም ዳይሬክተሩ አክለው ገልጸዋል፡፡
ሆኖም ማዕከላቱን ለመክፈት በሀገሪቱ ያሉ የአይን ብሌን ንቅለ ተከተላ ባለሙያዎች ቁጥር አነስተኛ መሆን አንዱና ዋነኛው ፈተና ሆኖ ቀጥሏል ሲሉ ጠቁመዋል፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘም ከአራትና አምስት ዓመታት በፊት አምስት ብቻ የነበሩትን ባለሙያዎች፤ አሁን ወደ 13 ማሳደግ ቢቻልም በሀገር አቀፍ ደረጃ ከሚያስፈልገው አንፃር አሁንም አነስተኛ ነው ብለዋል፡፡
ከዚህ ባሻገርም ሕብረተሰቡ የዓይን ብሌን ልገሳን በተመለከተ ያለው ግንዛቤ ዝቅተኛ መሆን፤ በአቅርቦቱ ላይ አሉታዊ ተፅእኖ እያሳደረ መሆኑን ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡
በዚህም አገልግሎቱ የተለያዩ የግንዛቤ ፈጠራ ስራዎችን እየሰራ ነው ያሉ ሲሆን፤ የሕዳር ወርንም የዓይን ብሌን ልገሳን አስመልክቶ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች የሚሰሩበት ነው ብለዋል፡፡
የኢትየጵያ ደምና ህብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት በትላንትናው ዕለት ከተለያዩ የሃይማኖት አባቶች፣ ከአባ ገዳዎችና ሐደ ስንቄዎች ጋር የዓይን ብሌን ልገሳ ወርን አስመልክቶ የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃ ግብር በአዳማ ከተማ አካሂዷል፡፡
አሐዱ ራዲዮ
