በአምባሳደር መለስ ዓለም (ዶ/ር) የተጻፈው “የኢትዮጵያና የኬንያ ስጋትና ተስፋ” የተሰኘ መጽሐፍ ተመረቀ። በ8 ምዕራፍ ተቀንብቦ በ306 ገጽ የቀረበው መጽሐፉ በኢትዮጵያና ኬንያ መካከል ያለውን ግንኙነት የሚዳስስና ፖለቲካዊ ብልሃቶችን ተንትኖ የሚያሳይ ነው።
በምርቃት ሥነ ሥርዓቱ ላይ የኢጋድ ዋና ጸሐፊ ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ፣የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታዎቹ አምባሳደር ብርሃኑ ጸጋዬ እና አምባሳደር ሃደራ አበራ፣በኢትዮጵያ የኬንያ አምባሳደርን ጨምሮ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አምባሳደሮች ፣ዲፕሎማቶች ፣የጸሐፊው ቤተሰቦች እና ወዳጆች እንዲሁም የቀድሞ የሥራ ባልደረቦች ታድመዋል።
በምርቃት ሥነ ሥርዓቱ ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሃደራ አበራ ባደረጉት ንግግር ልምድ ያካበቱ አምባሳደሮች እውቀታቸውን እና ልምዳቸውን ለትውልድ ለማስተላለፈ የአምባሳደር መለስ ዓለም(ዶ/ር)ን ፈለግ መከተል ይገባል ብለዋል።
ሚስትር ዴኤታው ጸሐፊው የኢትዮጵያ እና ኬንያ ግንኙነት ፣የጋራ ስጋት እና ተስፋን ከልምዳቸው በመነሳ በመጽሐፍ መሰነዳቸው ይበል የሚያሰኝ ነው ብለዋል።
የመጽሐፉ ጸሐፊ አምባሳደር መለስ ዓለም(ዶ/ር) በበኩላቸው መጽሐፍ ለመጻፍ ያነሳሳቸው ጉዳይ ያለፉበትን እና አገራቸውን ሲያገለግሉ ከቀሰሙት ልምድ እና ከገበዩት ዕውቀት በመነሳ ለትውልድ ለማስተላለፍ መሆኑን ገልጸዋል።
በሐጽሐፉ ምርቃት ሥነ ሥርዓት ላይ የቀድሞው አንጋፋ ዲፕሎማት አምባሳደር ተፈራ ሻወል እና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህሩ እና ተመራማሪው ዶ/ር ዮናስ አሽኔ ዳሰሳዊ ጽሑፍ አቅርበው ውይይት ተደርጎበታል።
አምባሳደር መለስ (ዶ/ር) ከዚህ ቀደም በጋዜጠኝነት ሙያ ያገለገሉና በኋላም በዲፕሎማሲ መስክ ተሰማርተው እያገለገሉ የሚገኙ ናቸው።
በመጽሐፍ ምርቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) ዋና ጸሐፊ ወርቅነህ ገበየሁን (ዶ/ር) ጨምሮ ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።
አምባሳደር መለስ ዓለም(ዶ/ር) መጀመሪያ በጋዜጠኝነት በአገሪቱ ግንባር ቀደም በሆኑት መገናኛ ብዙሃን ውስጥ በከፍተኛ ኃላፊነት የሰሩ ሲሆን በዲፕሎማሲ መስክም አገራቸውን ከሀያ ዓመት በላይ እያገለገሉ ነው።
የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቋንቋና ሥነ ጽሑፍ ያገኙ ሲሆን በትምህርቱ ዓለም የገፉበት መስክ ደግሞ ዓለም አቀፍ ግንኙነት እና ዲፕሎማሲ ነው። የሁለተኛ ዲግሪያቸውን ከናይሮቢ ዩኒቨርሲቲ፣የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ደግሞ ከስዊዘርላንድ የማኔጅመነት ዩኒቨርሲቲ በዓለም አቀፍ ግንኙነት ሰርተዋል።
ከከፍተኛ ዲፕሎማትነት በኬንያ ማላዊ እና ሲሸልሰ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሆነው አገራቸውን አገልግለዋል። በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል፣በጎረቤት አገራት ዳይሬክተር ጄኔራልነት እና በቃል አቀባይነት ያገለገሉ ሲሆን በአሁኑ ወቅት የአፍሪካ ጉዳዮች ምክትል ዳይሬክተር ጄኔራል ሆነው እየሠሩ ነው።
አምባሳደር መለስ ዓለም(ዶ/ር) ከአሁን በፊት በምሥራቅ አፍሪካ ላይ አተኩረው በሚሰሩ ጋዜጦች ላይ የአገራቸውን ጥቅም ያስቀደሙ እና ቀጣናዊ ትስስርን የሚያበረታቱ ጽሑፎችን አሳትመዋል።
በቴሌቪዥን መስኮቶች ቀርበው ስለ አገራቸው የውጭ ግኑኝነትኔ እና የአፍሪካ ቀንድ በርካታ ገንቢ አስተያዬቶችን በማቅረብ ይታወቃሉ።
በአሁኑ ወቅት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ምክትል ዳይሬክተር ጄኔራል በመሆን እያገለገሉ ነው።
