የኢትዮጵያ አየር መንገድ በግንባታ ላይ ከሚገኙት የአገር ውስጥ የአውሮፕላን ማረፊያዎች መካከል ሦስቱ ተጠናቀው በሚያዚያ ወር አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምሩ አስታወቀ።
አየር መንገዱ ባወጣው መረጃ መሠረት፣ የአገሪቱን የአየር ትራንስፖርት ተደራሽነት ለማስፋፋት እየተገነቡ ካሉ ፕሮጀክቶች ውስጥ ነገሌ ቦረና ፣ ጎሬ መቱ ፣ ደብረ ማርቆስ ፕሮጀክቶቹ ተጠናቀው በመጪው ሚያዚያ ወር 2018 ዓ.ም ይመረቃሉ።
አዳዲሶቹ ማረፊያዎች የንግድ እና የማኅበራዊ ትስስርን ከማጠናከራቸው ባለፈ፣ ለተጓዦች አማራጭና ቀልጣፋ ትራንስፖርት ለማቅረብ ያለሙ ናቸው።
አየር መንገዱ ከእነዚህ ሦስት ማረፊያዎች በተጨማሪ ሌሎች የኤርፖርት ግንባታዎችንና የማስፋፊያ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል።
“የእነዚህ አየር ማረፊያዎች መጠናቀቅ አየር መንገዱ ያለውን የአገር ውስጥ በረራ መዳረሻዎች ቁጥር ከማሳደጉም በላይ፣ ለየአካባቢው ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል” ሲል አየር መንገዱ አመልክቷል።
