ኢትዮጵያ “የትምህርት ቤቶች ደህንነት አዋጅ” የተሰኘውን የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት ደህንነት አዋጅ እንድታጸድቅ የመጠየቁን ሥራ በጋራ ለመስራት የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ጥያቄ አቅርቧል፡፡
በአማራ ክልል ብቻ አሁን ባለው ግጭት ምክንያት ከ4 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ውጪ የሆኑ ሲሆን፣ ከ3 ሺሕ 700 በላይ ትምህርት ቤቶች ከመማር ማስተማር ሥራ ውጪ ናቸው ተብሏል።
በተመሳሳይ በትግራይ ክልል ከ1 ነጥብ 2 ሚሊየን በላይ የሚሆኑ ተማሪዎች፤ አሁንም ወደ ትምህርት ቤት ተመልሰው ትምህርታቸውን መከታተል አለመጀመራቸውን የክልሉ ትምህርት ቢሮ ገልጿል።
ይህንንም ተከትሎ የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት ደህንነት አዋጅን እንድታጸድቅ ጥያቄ ለማቅረብ ከኢትዮጵያ ሴቶች ፌደሬሽን ጋር በጋራ ለመስራት ጥሪ አቅርቧል።
የማህበሩ ፕሬዝዳንት ዮሐንስ በንቲ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ በትምህርት በሴቶች እንዲሁም በሴት ተማሪዎች ዙሪያ ድምጽ ለመሆን ከኢትዮጵያ ሴቶች ፌደሬሽን ጋር በጋራ መሰራት እንዳለበት ገልጸዋል።
በዚህም በሁሉም የትምህርት ተቋማት ሰላማዊ የመማር ማስተማር አካባቢ እንዲኖር ለማስቻል፤ ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት ደህንነት አዋጅን ተቀብላ እንድታጸድቅ ሥራዎችን በጋራ ለመስራት ለፌደሬሽኑ ጥሪ አቅርበዋል።
ይህ አዋጅ ትምህርት ቤቶች ከግጭት ነጻ እንዲሆኑና ጥበቃም እንዲደረግላቸው የሚጠይቅና የሚያሳስብ መሆኑን ገልጸው፤ አሁን በትምህርት ቤቶች ላይ የሚስተዋለውንና በግጭት ምክንያት የሚደርሰውን ጫና ለመከላከል የሚያግዝ መሆኑንም አንስተዋል።
“የትምህርት ቤቶች ደህንነት አዋጅ” የተሰኘው በመንግሥታቱ ድርጅት የተረቀቀውን ዓለም አቀፍ ሕግ እስካሁን ያጸደቁት 120 ሀገራት ብቻ ሲሆኑ፤ ተጨማሪ የተመድ አባል ሀገራት አዋጁን በሀገራቸው ሕግ አውጪ ምክር ቤት አጸድቀው የትምህርት ቤቶችን ደህንነት እንዲያስከብሩ ድርጅቱ ጥሪ ማቅረቡ ይታወቃል።
