እውነተኛው ንጉሱና ተተኪው የተገናኙበት የበጎ አድራጎቱ ዕጣ ፋንታ !

Date:

በቅርቡ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ በስፋት ሲዘዋወር የነበረውና የብዙዎችን ቀልብ የሳበው የሊዮኔል ሜሲ እና የላሚን ያማል የድሮ ፎቶ እውነተኛ መሆኑ ተረጋግጧል።

ይህንን እውነታ የተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) ያረጋገጠው ሲሆን፣ ፎቶው ከተራ ምስልነት ባለፈ የሁለት ትውልድ እግር ኳስ ድንቆችን እጣ ፈንታ አስቀድሞ ያቆራኘ አስገራሚ ታሪካዊ ቅጽበት ሆኖ ተመዝግቧል።

ይህ ታሪካዊ ፎቶግራፍ የተነሳው  በ2007 በባርሴሎናው ካምፕ ኑ ስታዲየም የልብስ መቀየሪያ ክፍል ውስጥ ነበር።

የባርሴሎናው ታዋቂ ጋዜጣ ዲያሪዮ ስፖርት ከዩኒሴፍ ጋር በመተባበር ለበጎ አድራጎት የገቢ ማሰባሰቢያ ቀን አዘጋጅቶ ነበር። በወቅቱ በሮካ ፎንዳ ይኖሩ የነበሩት የላሚን ያማል ወላጆች በዩኒሴፍ በተዘጋጀው ዕጣ ላይ በመሳተፍ፣ ልጃቸው ከባርሴሎና ተጫዋች ጋር የመገናኘት ዕድል አገኘ።

በወቅቱ ሊዮኔል ሜሲ ገና የ20 ዓመት ወጣት የነበረ ሲሆን፣ በዓለም እግር ኳስ ላይ ገና አሻራውን ማሳረፍ የጀመረበት ወቅት ነበር።

ፎቶውን ያነሳው  ዕውቁ የፎቶ ጋዜጠኛ ጆአን ሞንፎርት ሲሆን አጋጣሚውን ሲያስታውስ  ሜሲ አይነ-አፋር ከመሆኑ የተነሳ ገና የአምስት ወር ህጻን የነበረውን ያማልን በገንዳ ውስጥ እንዴት አቅፎ ማጠብ እንዳለበት ግራ ገብቶት ነበር በማለት ያስታውሳል።

ከ18 ዓመታት በፊት ላሚን ያማል ገና ህጻን እያለ፣ ከእናቱ ሺላ ጋር በመሆን በዩኒሴፍ የገቢ ማሰባሰቢያ የፎቶ መርሃ-ግብር ላይ ከእግር ኳስ ንጉሱ ሊዮኔል ሜሲ ጋር መገናኘቱ ዛሬ ላይ ትልቅ ትርጉም ሰጥቶታል።

ዛሬ ሁለቱም በሜዳ ላይ በሚያሳዩት ድንቅ ስኬታቸው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን እያነሳሱ ይገኛሉ።

ሜሲ ስምንት የባሎንዶር ሽልማቶችን በማሸነፍ በታሪክ ታላቁ ተጫዋች መሆኑን ሲያስመሰክር፣ ያማል ደግሞ በታዳጊነቱ ስፔንን ለአውሮፓ ዋንጫ ድል በመምራትና በባርሴሎና ቤት አዲስ ኮከብ በመሆን የሜሲን ፈለግ እየተከተለ ይገኛል።

ይህ ትስስር በሜዳ ላይ በሚታይ ድንቅ ብቃት ብቻ የተገደበ አይደለም። ከሜዳ ውጪም ሜሲ እና ያማል የዩኒሴፍ የበጎ ፈቃድ አምባሳደሮች በመሆን፣ በመላው ዓለም ለሚገኙ ህጻናት መብት መከበርና ደህንነት ድምጻቸውንና ስማቸውን በበጎ ተግባር ላይ እያዋሉ ይገኛሉ።

የዩኒሴፍ ዋነኛ ዓላማ እያንዳንዱ ህጻን እንዲተርፍ፣ እንዲያድግና ሙሉ አቅሙን እንዲጠቀም ማስቻል ሲሆን፤ ድርጅቱም እነዚህን ሁለት ታላላቅ የዓለም እግር ኳስ ኮከቦች በአንድ ወቅት በበጎ አድራጎት መድረኩ ላይ በማገናኘቱና ዛሬም በቡድኑ ውስጥ በማካተቱ ታላቅ ኩራት እንደሚሰማው ገልጿል።

በሊዮኔ ሜሲ እጅ ገና በአምስ ወሩ የተዳሰሰው ላሚን ያማል አሁን በትልቁ የዓለም ዋንጫ መድረክ ፍጻሜ በ20 ዓመት ከሚበልጠው እና ከሚያደንቀው ኮከብ ጋር ፊት ለፊት የሚፋጥበትን ዕድል አግኝቷል።

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

ጄኤፍኤም 106.7 የሬዲዮ ጣቢያ ለ6 ወራት ታገደ

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ባደረገው የይዘት ክትትልና የኢንስፔክሽን ምልከታ...

ሱልጣን ቢን ኻሊፋ ግሩፕ በኢትዮጵያ በሆቴል ዘርፍ ሊሰማራ ነው

በተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች የኢፌዲሪ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር...

የአሜሪካ የታክስ ህግ የስፔንን የዓለም ዋንጫ ሽልማት ስጋት ላይ ጣለ

የስፔን ብሔራዊ ቡድን ከዓለም ዋንጫ ሊያገኘው ከሚችለው 50 ሚሊዮን...

ህወሓት ከሌሎች ተቃዋሚ ኃይሎች ጋር የሚደረግ ጥምረት አስፈላጊ መሆኑን ገለጸ

ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ...