የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ባለውና ከክልል እስከ ወረዳ ያሉ የመንግሥት አመራሮች በሚሳተፉበት መድረክ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ኦሮሚያ ክልል “ጠፍቶ” ለማየት የሚመኙና ኦሮሚያ የሚለውን ቃል መስማት የማይፈልጉ አካላት አሉ ሲሉ ገልጸዋል።
ይህ ምኞት “በፍጹም” ሊሳካ እንደማይችል የገለጹት ርዕሰ መሥተዳድሩ፣ ይልቁንም ክልሉ ወደፊት ይበልጥ እየጠነከረ፣ መሬት እየያዘና ውጤታማ እየሆነ እንደሚሄድ በኦሮምኛ ቋንቋ ባደረጉት ንግግር አመልክተዋል፡፡
ርዕሰ መሥተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ኦሮሚያ ክልል ጠፍቶ ማየት ይፈልጋሉ ያሏቸውን አካላት ማንነት ግን በስም ለይተው በንግግራቸው ውስጥ አልጠቀሱም።
አቶ ሽመልስ ይህን የተናገሩት፣ የክልሎች አወቃቀር ጉዳይ ለአገራዊ ምክክር ጉባኤው በአጀንዳነት በቀረበበት ማግስት ነው።
