የህዳሴ ግድቡ ውዝግብ በፖለቲካዊ ሳይሆን በቴክኒካዊ መንገድ መፈታት አለበት

Date:

በአሜሪካ ውጪ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የአፍሪካ፣ እና የመካከለኛው ምስራቅ ጉዳዮች ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት ማሳድ ቡሎስ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ ያለው ውዝግብ “በፖለቲካዊ ጫና ሳይሆን በቴክኒካዊ መንገድ መፈታት አለበት” ሲሉ ተናገሩ።

ማሳድ ቡሎስ ከአል-ዓረቢያ ቴሌቪዥን ጋር በነበራቸው ቃለ-ምልልስ፣ ዋሽንግተን በሦስቱ አገራት ማለትም በኢትዮጵያ፣ በሱዳን እና በግብፅ መካከል ሰላማዊ እና ሁሉን አቀፍ ተቀባይነት ያለው መፍትሔ ለማምጣት ያላትን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።

“ጉዳዩ የቴክኒክ ጉዳይ በመሆኑ፣ ችግሩ በቴክኒካዊ መንገዶች ነው መፈታት ያለበት” ያሉት ከፍተኛ አማካሪው፤ “በተለይም በቴክኒካዊ ጉዳዮች ለሁሉም ወገኖች ተስማሚ መፍትሔ ለማግኘት እየሰራን ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

“ጉዳዩ ለኢትዮጵያ፣ ግብፅ እና ሱዳን የሞትና የሕይወት ጉዳይ” መሆኑን የጠቀሱት ማሳድ ቡሎስ፤ “ግዙፉ የውሃ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ተመርቆ እውን ሆኗል፤ ወደፊት የሚካሄዱ ማናቸውም የመፍትሔ አካሄዶችም ይህን እውነታ ያገናዘቡ መሆን አለባቸው” ሲሉ አሳስበዋል።

አክለውም ሀገራቸው በካይሮ እና አዲስ አበባ መካከል ሰላማዊ ትብብርን መደገፏን ትቀጥላለች ያሉ ሲሆን፤ ሁለቱን ሀገራት [ግብፅ እና ኢትዮጵያ] “ወደ ግጭት ማምራት የሌለባቸው እና በታሪካዊ ትስስር የተቆራኙ ሀገራት” ሲሉ ገልጸዋቸዋል።

ከፍተኛ አማካሪው በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያና ግብፅ አድርገውት በነበረው ጉብኝት ወቅት የህዳሴ ግድቡ ጉዳይ ዋነኛ ትኩረት እንደነበረ ገልፀው፤ በአሜሪካና በግብፅ መካከል ንግግሮች መቀጠላቸውን አመልክተዋል።

ቡሎስ፣ የህዳሴ ግድቡ ጉዳይ ለፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ “በጣም አስፈላጊና ስትራቴጂካዊ” እንደሆነ ገልፀው፤ በመጀመሪያው የፕሬዝዳንትነት ዘመናቸውም ለጉዳዩ መፍትሔ ለመፈለግ ጠንክረው መስራታቸውን አስታውሰዋል።

አክለውም ለቀጣይ ውይይት እና ድርድሮች ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የግብፁን ፕሬዝደንት አብደል ፋታህ አል ሲሲ እና የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ለማሸማገል ይፈልጉ እንደሆን የተጠየቁት ማሳድ ቡሎስ፤ “ፈጣሪ ከፈቀደ አብረው ሆነው እናያቸዋለን። እኛም ለዚሁ ግብ እየሰራን ነው” ብለዋል።

የግብፁ ፕሬዝዳንት አብዱል ፋታህ አል ሲሲ ከትናንት በስተያ እሁድ ግብፅ “ኢትዮጵያ በግድቡ ላይ የምታደርገው የተናጥል የውኃ አጠቃቀም ያልተገባ እና ኃላፊነት የጎደለው ነው፤ የግብፅን የውሃ ጥቅሞች ለማስጠበቅም ሁሉንም አስፈላጊ እርምጃዎች” ትወስዳለች ሲሉ መግለጻቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

ይህን ተከትሎ የኢትዮጵያ ውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ትናንት ሰኞ ጥቅምት 3/2018 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ፤ ግብፅ በዓባይ ወንዝ እና በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ “ፀብ አጫሪ ንግግሮችን” አጠናክራ ቀጥላለች ሲል ከሷል። የካይሮ “የቅኝ ግዛት ዘመን አስተሳሰብ” በዓባይ ተፋሰስ አገሮች መካከል ያለውን አከባቢያዊ ትብብር አደጋ ላይ ይጥላል ሲልም አስጠንቅቋል።

ሚኒስቴሩ በመግለጫው “ኢትዮጵያ የዓባይን ወንዝ የመጠቀም መብቷን እንድትተው በሚደረግ ግፊት አትሸበርም” ሲል ገልጾ፤ የግብፅን አቋም “ትብብርን ከማጎልበት ይልቅ ኢትዮጵያን ለማዳከም ያለመ የከሸፈ ፖሊሲ” ሲል ወቅሶታል።

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

አክሊሉ ወንድሞቹ ለንባብ በቃ

በፀሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ የልጅነት ታሪክ ላይ ያተኮረ ለታዳጊዎች...

የኢራን ተፈጥሮአዊ ምሽጎች እና ስትራቴጂካዊ ጥበብ

​ግዮን መጽሔት :- በመካከለኛው ምስራቅ የጂኦ-ፖለቲካ ትኩሳት...

ለአድዋ ድል መታሰቢያ በአሜሪካ ቀን ተሰየመ

በአሜሪካ፣ የፔንሲልቪኒያ ግዛት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ የአውሮፓዊያኑ 'መጋቢት...

ኢሎን መስክ የዓለማችን የመጀመሪያው ትሪሊዮነር ሆነ

ኢሎን መስክ የሀብት መጠኑ 1 ትሪሊዮን ዶላር ያለፈ የመጀመሪያው...