በመካከለኛው ምስራቅ እየተባባሰ የመጣው ጂኦፖለቲካዊ አለመረጋጋት ለኢትዮጵያ አየር መንገድ አዲስ የገበያ ዕድል ፈጥሯል።
በእስራኤል-አሜሪካ እና በኢራን መካከል ያለው ግጭት በባህረ ሰላጤው አገራት የአየር ትራንስፖርት ላይ መስተጓጎል በመፍጠሩ፣ የደቡብ አፍሪካ መንገደኞች አዲስ አበባን እንደ ዋነኛ የመሸጋገሪያ ማዕከል እየተጠቀሙባት ይገኛሉ።
የኢንዱስትሪ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ ከመጋቢት ወር መጀመሪያ ጀምሮ በኢትዮጵያ አየር መንገድ በኩል የሚደረጉ የቦታ ማስያዝ (Bookings) መጠኖች በድንገት የ110% ጭማሪ አሳይተዋል።
የFlight Centre South Africa የሥራ ኃላፊ ሱ ጋሬት፣ ይህ ለውጥ የመጣው በተለመዱት የበረራ መስመሮች ላይ በተፈጠረው ስረዛ እና የአየር ክልል ገደቦች መሆኑን ገልጸዋል።
የዓለም አቀፉ የአየር ትራንስፖርት ማህበር (IATA) መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አሁን ካለው ቀውስ በፊትም ቢሆን በቁልፍ የጉዞ መስመሮች ላይ የበላይነቱን እያጠናከረ መቆየቱን ያረጋግጣሉ።
ለአብነትም በ2025 ብቻ በጆሃንስበርግ-ሙምባይ መስመር በአዲስ አበባ በኩል ከ69,000 በላይ መንገደኞችን በማጓጓዝ ወደ ሕንድ ለሚደረጉ በረራዎች ቀዳሚው ምርጫ መሆን ችሏል።
በተመሳሳይ በብሪታንያ እና በደቡብ አፍሪካ መካከል ባለው የጉዞ መስመር ኤምሬትስን በ39,000 መንገደኞች በመብለጥ ትልቁ ቀጥተኛ ያልሆነ አጓጓዥ ለመሆን በቅቷል።
በተጨማሪም በደቡብ አፍሪካ እና በአሜሪካ መካከል በሚደረግ የጉዞ እንቅስቃሴ፣ አየር መንገዱ ከዩናይትድ እና ከዴልታ በመቀጠል በሦስተኛ ደረጃ ላይ በመቀመጥ ጠንካራ የገበያ ተወዳዳሪነቱን አስመስክሯል።
