የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ትራምፕ ስደተኞችን ወደ ሦስተኛ አገር እንዲያባርሩ ፈቀደ

Date:

የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የፕሬዝዳንት ትራምፕ አስተዳደር ስደተኞችን ከአገራቸው ባለፈ ወደ ሦስተኛ ሀገር ማባረረ እንዲችል ፍቃድ ሰጥቷል።

በዚህም የታችኛው ፍርድ ቤት የትራምፕ አስተዳደር ስደተኞች ወደ ሦስተኛ አገር ሲባረሩ የሚገጥማቸውን ችግር እንዲያስረዱ “ትርጉም ያለው እድል” እንዲሰጥ የወሰነውን ውሳኔ፤ ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ስድስት ለሦስት በሆነ ድምፅ መሻሩ ነው የተገለጸው።

ሦስት ለዘብተኛ የፍርድ ቤቱ ዳኞች ” ሕገ ወጥነትን የሚያበረታታ ነው” ያሉትን ብይን ተቃውመዋል።

ጉዳዩ ባለፈው ግንቦት የምያንማር፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኩባ፣ ሜክሲኮ፣ ላኦስ እና ቬትናም ስምንት ስደተኞችን ወደ ደቡብ ሱዳን የሚወስድ አውሮፕላን ውስጥ እንዲሳፈሩ መደረጉን ተከትሎ የመጣ መሆኑን፤ ቢቢሲ በዘገባው አመላክቷል።

የቦስተን የአሜሪካ ፍርድ ቤት ዳኛ ብራየን መርፊ ባለፈው ሚያዚያ ስደተኞቹ ‘በሦስተኛ ሀገር ማሰቃየት ወይንም ግድያ ይፈፀምብናል’ ብለው ካመኑ፤ ጉዳያቸውን እንዲያሰሙ ዕድል ሊሰጣቸው እንደሚገባ ውሳኔ አሳልፈው እንደነበር ይታወሳል።

ዳኛ ሶኒያ ሶቶማየር፣ ኢሌና ኬጋን እና ኬትማጂ ብራውን ጃክሰን ሰኞ ዕለት በአብላጫ ድምፅ የፀደቀውን እና ያልተፈረመውን ውሳኔ “ከባድ ጥሰት” ሲሉ መተቸታቸውን ዘገባው አመላክቷል።

የአሜሪካ የአገር ውስጥ ደኅንነት መስሪያ ቤት ውሳኔው “ለአሜሪካ ሕዝቦች ደኅንነት እና ጥበቃ ድል ነው” ያለ ሲሆን፤ የተቋሙ ቃል አቀባይ ትሪሺያ ማክሊን “ማባረሪያ አውሮፕላኖች ያሟሙቁ” ሲሉ ከውሳኔው በኋላ ተናግረዋል።

የትራምፕ አስተዳደር “ስምንቱ ስደተኞች በአሜሪካ ግድያ፣ እሳት ቃጠሎ እና በጦር መሳሪያ ዝርፊያን ጨምሮ “አስከፊ ወንጀሎችን” የፈፀሙ ናቸው” ብሏል።

የስደተኞቹ ጠበቃ ለጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ባስገቡት ማመልከቻ፤ “አብዛኞቹ ስደተኞች ወንጀለኛ ተብለው የተፈረደባቸው አይደሉም” ብለዋል።

ከሳሾቹን የወከለው ብሔራዊ የኢሚግሬሽን ሙግት ትብብር የፍርድ ቤቱን ውሳኔ “አስፈሪ” ሲል የጠራው ሰሆን፤ የትብብሩ ሥራ አስፈፃሚ ትሪና ሪልሙቶ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ደንበኞቻቸውን “ለስቃይ እና ሞት” ያጋለጠ እንደሆነ ተናግረዋል።

ትራምፕ ጉዳዩን ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የወሰዱት የታችኛው ፍርድ ቤት የወሰነውን ባለፈው ወር የቦስተን ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ውሳኔውን ባለመቀልበሱ ነው።

በባይደን የተሾሙት ዳኛ ብራየን መርፊ የአሜሪካ መንግሥት ስደተኞች ወደ ሦስተኛ አገር ሳያባርር የአሜሪካ የጦር ሰፈር ባለበት ጅቡቲ እንዲያቆዩ ጠይቀዋል።

ባለፈው ወር ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ 350 ሺሕ ስደተኞች ላይ ተፅዕኖ የሚያሳርፍ እና ለቬኑዚዌላ ዜጎች ተሰጥቶ የነበረውን ጊዜያዊ ጥበቃ እንዲነሳ ውሳኔ አሳልፏል።

በሌላ ውሳኔ ባለፈው ግንቦት ወር ግማሽ ሚሊዮን ለሚሆኑ የኩባ፣ ሄቲ፣ ኒካራጉዋ እና ቬንዙዌላ ስደተኞች ለሁለት ዓመት በአሜሪካ ሲቆዩ የሚሰጣቸውን የሰብዓዊ ድጋፍ ፕሬዝዳንቱ በጊዜያዊነት እንዲያቋርጡ መወሰኑም ተዘግቧል።

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

አክሊሉ ወንድሞቹ ለንባብ በቃ

በፀሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ የልጅነት ታሪክ ላይ ያተኮረ ለታዳጊዎች...

የኢራን ተፈጥሮአዊ ምሽጎች እና ስትራቴጂካዊ ጥበብ

​ግዮን መጽሔት :- በመካከለኛው ምስራቅ የጂኦ-ፖለቲካ ትኩሳት...

ለአድዋ ድል መታሰቢያ በአሜሪካ ቀን ተሰየመ

በአሜሪካ፣ የፔንሲልቪኒያ ግዛት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ የአውሮፓዊያኑ 'መጋቢት...

ኢሎን መስክ የዓለማችን የመጀመሪያው ትሪሊዮነር ሆነ

ኢሎን መስክ የሀብት መጠኑ 1 ትሪሊዮን ዶላር ያለፈ የመጀመሪያው...