የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባካሄደው የውጪ ምንዛሪ ጨረታ፣ የኢትዮጵያ ብር ከአሜሪካን ዶላር ጋር ያለው የምንዛሪ ተመን በከፍተኛ ደረጃ መዳከሙ ታውቋል። ይህ ለውጥ በተለይ ባለፉት ሁለት ወራት ውስጥ የገበያውን መረጋጋት ለመደገፍ በተዘጋጀው የጨረታ መድረክ ላይ የሚታይ ትልቅ ጭማሪ ነው።
ህዳር 23 ቀን 2018 ዓ.ም. በተካሄደው 11ኛዉ ዙር የውጪ ምንዛሪ ጨረታ፣ ለአንድ የአሜሪካን ዶላር አማካይ የምንዛሪ ተመን ብር 154.3993 ሆኖ ተመዝግቧል። በዚህ ዙር 17 ባንኮች የውጭ ምንዛሪ ድልድል ማግኘታቸውን ካፒታል ተመልክቷል።
ከአንድ ወር በፊት፣ ጥቅምት 04 ቀን 2018 ዓ.ም. በተካሄደው 10ኛዉ ዙር ጨረታ የአንድ ዶላር አማካይ ተመን 148.1007 ብር ነበር። ይህ ማለት ብሩ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ በአማካይ 4.25% በዶላር ላይ መዳከምን አሳይቷል።
ከሁለት ወራት በፊት በ9ኛው ዙር ጨረታ የተመዘገበው አማካይ ተመን 138.2 ብር እንደነበር ይታወሳል። ከዚህ ተመን ጋር ሲነፃፀር፣ የዶላር ዋጋው በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመር በሁለት ወራት ውስጥ የ11.72% የምንዛሪ ተመን ጭማሪ ታይቷል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ በጨረታ ማቅረቡን የገበያውን መረጋጋት ለመደገፍ ያለመ ቢሆንም፣ የብር ተመን ፈጣን መዳከም ግን የገንዘብ ገበያው ምን ያህል ፈጣን ለውጥ እያስተናገደ እንደሆነ የሚያሳይ መሆኑ ተጠቁሟል።
capital news
