የትግራይ ክልል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዜዳንት ፀጋይ ብርሃነ ገ/ተኽለ እና ምክትላቸው ገብረኣምላኽ የዕብዮ ከስራ ገበታቸው ተሰናብተዋል።
በትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር ፕሬዜዳንት ታደሰ ወረደ (ሌ/ጀነራል) ፊርማ ግንቦት 5/2017 ዓ.ም የተፃፈው ደብዳቤ እንደሚያመለክተው ፥ ፕሬዜዳንቱና ምክትላቸው የስራ መልቀቅያ እንዲሰጣቸው በጠየቁትና ባመለከቱት መሰረት ከምስጋና ጭምር ስንብት ተሰጥቶዋቸዋል።
በዚህም ፕሬዜዳንቱና ምክትላቸው ከዛሬ ግንቦት 6/2017 ዓ.ም ጀምሮ ከስራ መሰናበታቸው የተፃፈላቸው ደብዳቤ ያመለክታል።
ፕሬዜዳንቱ እና ምክትላቸው የቀድሞ ፕሬዜዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ወደ ስልጣን መምጣታቸው ተከትሎ ወደ ሃላፊነት የመጡ ሲሆን ከአንዴም ሁለቴ ጊዜ ስራ ለመልቀቅ ጠይቀው ሳይሳካላቸው ቀርቷል።
የስራ መልቀቅያ እንዲያስገቡ እንደ ምክንያት ከጠቀሱዋቸው ችግሮች የጊዚያዊ አስተዳደሩ ስራ አስፈፃሚ አካላት በህግ ልዕልና የሚያሳዩት ያልተገባ ጣልቃ ገብነት መሆኑን ከዚህ ቀደም መግለጻቸውን ቲክቫህ ኢትዮጵያ መረጃ ማድረጉ ይታወሳል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ
መቐለ
