“የያዝነው ሀሳብ ኢትዮጵያን ስለሚጠቅማት የሚረዳን አካል እንፈልጋለን”

Date:

ግዮን መጽሔት ከአቶ ወንድምነው ንብረት ጋር የነበራትን ቆይታ በዚህ የመጨረሻ ክፍል ተጠናቅቋል ።

ግዮን፡- ስለ ሥራችሁ ሕዝቡ ያለው ተቀባይነት ምን ይመስላል?


ወንድምነው፡-በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል ተቀባይነቱ እጅግ ደስ ሚያሰኝ ነው፡፡ ምክንያቱም ህብር ኢቲ የያዛቸው ፕሮጀክቶች ዘመኑን የዋጁና እጅግ ተፈላጊ ናቸው፡፡


ግዮን፡- በቅርቡ ግንቦት 10 ቀን 2017 ዓ.ም የምታደርጉት ፕሮግራም ምንድን ነው?


ወንድምነው፡- ግንቦት 10 ቀን 2017 ዓ.ም የሚካሄድ ትልቅ ፕሮግራም አለን፡፡ ሕብር ኢቲ ብድርና ቁጠባ አጠቃላይ ፕሮግራም ያካሂዳል፡፡ ይሄ ፕሮግራም ትልቅ ዝግጅት የተደረገበት ነው፡፡ የእኛ ሠራተኞች በትጋት ነው የሚሠሩት፡፡ ተቋሙ ወደፊት በሀገራችን ብዙ ሰው የሚረከበው ነው፡፡

ያ እንዲሆን ነው ሠራተኞቻችን ያለእንቅልፍ በትጋት የሚሠሩት፡፡ የብድርና ቁጠባ ተቋማችን ገና በ6ኛ ወሩ ነው የመኪናና ሌሎች ልዩ ልዩ ብድሮችን የሚሰጠው፡፡ ይህም የሚከናወነው ግንቦት 10 ቀን 2017 ዓ.ም ነው፡፡ ተቋማችን ሕዳር 10 ቀን 2017 ዓ.ም. ተቋቁሞ ግንቦት 10 /2017 ላይ በይፋ የመኪኖችን ቁልፍ የሚያስረክብበት ሂደት ነው ያለው፡፡ ይኼ ትልቅ ስኬት ነው፤ በጣም ብዙ ዋጋ ከፍለናል፡፡ በእለቱ የተለያዩ ብድሮችን የወሰዱ አካላት የምናስተዋውቅበትም ነው፡፡ ይኼ ለአባሎቻችን የከፍለነው ትልቅ ዋጋ ነው፡፡


ሀገራችን ሠጥቶ መቀበል የሚል መርህ ያስፈልጋታል፡፡ እኛም ይህን መርህ ተከትለን ነው የምንሠራው፡፡ በሀገራችን ዓመታትን ያስቆጠሩ የእኛን መሰል ተቋማት አሉ፡፡ ነገር ግን ወደፊት መራመድ አልተቻላቸውም፡፡

ከዚህ አንጻር ሕብር ኢቲ ሁለት ሲስተሞችን ይዞ መጥቷል፡፡ የመጀመሪያው በጣም ማስታወቂያ ይሠራል፡፡ ለብዙዎች የማስተዋወቅ የሥራ እድል ፈጥሯል፡፡ ተቋማችንን ተንትነው ባስረዱት ልክ ኮሚሽን ያገኛሉ፡፡ ተቋሙ ብቻውን አይጠቀምም፡፡ ኮሚሽን ሲከፍል የሥራ እድል እየፈጠረ ነው፡፡ ሲያሠለጥን ሰው እየገነባ ነው፡፡

የማይሠሩ ሰዎች አክስዮን ገዝተው እንዲሄዱ ይደረጋል፡፡ ለሚሠሩ ሰዎች ደግሞ ጥቅም ያጋራል፡፡ ድርጅቱ አሠልጥኜ ልስደድ አይልም፡፡ ድርጅቱ እራሱን በማኅበራዊ ሚዲያም ማስተዋወቅ ይችላል፡፡ ነገር ግን ሁሉም መጠቀም ስላለበት ለዚያ የሚሆን ሲስተም ዘርግቷል፡፡ ድርጅቱ በዚህ ዙሪያ የሚሠራ የራሱ ሶፍትዌር አዘጋጅቷል፡፡ ሂሳብ ሠርቶ ለየትኛውም አካል የሚሰጠው ይህ ተቋማችን ያዘጋጀው ሶፍትዌር ነው፡፡


ግዮን፡- ዲጂታል እቁብ ምን ማለት ነው?


ወንድምነው፡- ዕቁብ ማለት አንድ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች ዕለታዊ ፍጆታቸውን ለመሙላት ገንዘብ ሰብስበው የሚጥሉበት ሂደት ነው፡፡ ሰዎች የአንዱን ለአንዱ እየሰጡ ችግራቸውን የሚፈቱበት ሂደት ነው፡፡
እኛ ይህ እቁብ ድርጅታዊ ቅርጽ እንዲኖረው ነው ያደረግነው፡፡ ሲስተም ፈጥረን በዚያ ሲሰተም አማካኝነት ነው የሚጣለው፡፡

እኛ በወረቀት አጣጥለን ሳይሆን እጣ የምናወጣው በቴክኖሎጂ ታግዘን ነው፡፡ ራሱ ቴክኖሎጂው ሰዎችን በወረፋቸው ያስተናግዳል፡፡ ይህ ሲስተም የአምስት ዓመት እቅድ አለው፡፡ በዚህ አምስት ዓመት ውስጥ ማንም ሰው መጥቶ መጣል ይችላል፡፡

አምስት ዓመት እቁብ ከብዛት አንፃር ረጅም አይደለም፡፡ እኛ ጋር እቁብ የሚጥለው መቶና ሁለት መቶ ሰው አይደለም፡፡ በጣም ብዙ ሰው ነው፡፡ ስለዚህ አምስት ዓመት ረጅም አይደለም፡፡ ከአምስት ዓመት በኋላ ደግሞ ክፍል ሁለት እቁብ ይጀመራል፡፡ እኛ ጋር ከእቁቡ ላይ ትንሽ ፐርሰንት ተቀማጭ ይደረጋል፡፡

ይህ የሚደረገው በመጀመሪያ ደረጃ እቁብ በልቶ የሚጠፋ ወይም የሚያቋርጥ ሰው ካለ የእሱን ቦታ በዚያች ብር ለመሸፈን ነው፡፡ ነገር ግን የሚያቋርጥ ወይም የጠፋ ሰው ከሌለ ተቀማጩን ገንዘብ ተሰልቶ ለአባላቱ ይከፋፈላል፡፡ ይህን ሲያደርግ ግን የእቁብ አባላቱን አካታች ያደረገ የተለያዩ የኢንቨስትመንት ሥራዎችን ይሠራል፡፡ እስካሁን ከ300 በላይ ሰው እቁብ ደርሶታል፡፡


ግዮን፡- በኢንቨስትመንት ሥራ ውስጥ ወደፊት እቅዳችሁ ምንድን ነው?


ወንድምነው፡- እንደተቋም የምንሠራው ሥራ ብዙ ነው፡፡ ለአባላቱ የኢንቨስትመንት ተቋም ማሳደግ የድርጅታችን ዋና ሥራ ነው፡፡ ሕብር ኢቲ በኦንላየን ቢዝነስ ሳይሆን የሚያምነው በተግባር በተሠራ ቢዝነስ ነው፡፡ ለምሳሌ ፋይናንስ ከሆነ ድርጅታችን እንሠልጥን፣ እንቆጥብ እና እናልማ የሚል መርህ ነው ያለው፡፡

ነገር ግን ይህ የተግባር ሥራ የሚመራው ዲጂታላይዝድ ሆኖ በቴክኖሎጂ ነው፡፡ በሕብር ኢቲ ውስጥ አባል የሆነ ማንም ሰው የኢንቨስትመንት አክስዮን መግዛት ይችላል፡፡ አብዛኛው የእኛ ሥራ ግብርና ላይ ያተኮረ ነው፡፡ በሌሎች ሀገሮች በግብርናው ዓለም የሚኖሩ ሰዎች በሀብት የመጠቁ በዘመናዊነታቸው የተመነደጉ ናቸው፡፡ ሀገራችን የሚገርም ለም አፈር ያላት ሀገር ናት፡፡


ቡና፣ ማንጎ፣ አኩሪአተር ሰሊጥና መሠል አዝዕርቶች ላይ ሁሉ ቢሠማሩ ውጤታማ መሆን የሚቻልባት ነች፡፡ እንዲህ ዓይነት ኢንቨስትመንቶች ላይ መሰማራት ሀገርንና መንግሥትን ማገዝ ነው፡፡ ሀገሪቷ አምራች ትፈልጋለች፡፡

ሀብቷ ዝም ብሎ ተበትኖ ነው ያለው፡፡ ጥርት ያለ ሥራ የሚያከናውን ዜጋ ያሻታል፡፡ የእኛ ተቋም የሚጥረው ያንን ለመሸፈን ነው፡፡ በሥራ አካባቢያችን ያለው አካል ሁሉ የሥራ እድል ይፈጥራል፡፡ በሥራው አርአያ ይሆናል፤ ስለዚህ በተለይ በግብርና ሥራው ላይ እና አስመጪና ላኪነት ላይ እንዲሁም ትራንስፖርት ኮንስትራክሽን ላይ እየሠራን ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ሥራዎች ለአባላቶቻችን በጣም ይጠቅማሉ፡፡

ትኩረት የምናደርገው ሕዝብ ላይ ውጤት ሊያመጣ የሚችል ሥራ ላይ ነው፡፡ የሕዝብን እውቀት የሕዝብን አቅምና ሀብት በቀላሉ ልንጠቀምበት የምንችለውን መንገድ እንከተላለን፡፡ የሥራ እድል መፍጠር የሚችል ሥራ ነው የምናከናውነው፡፡ ለምሳሌ የሆቴልና ቱሪዝም መክፈት በዕቅዳችን ውስጥ ያለ ነው፡፡ እያንዳንዱ ሥራ ከመሥራታችን በፊት ይበልጥ ለሀገርና ለሕብረተሰቡ የሚጠቅመውን ጥናት እናደርጋለን፡፡


ግዮን፡- ማኅበራዊ ኃላፊነታቸሁን ከመውጣት አንጻር የሠራችሁት ነገር አለ?


ወንድምነው፡- በ2018 ዓ.ም እንደፈጣሪ ፈቃድ በዚህ ዙሪያ ብዙ ሥራ እንሠራለን ብለን እናምናለን፡፡ ድርጅታችን ትልቁን እርካታ የሚያገኘውም ማኅበራዊ አገልግሎት በመስጠት ነው፡፡ አሁን ደግሞ እንደ ድርጅት ይህን ተግባር ወርደን እንሠራዋለን፡፡

ድርጅታችን ከተቋቋመ ስድስት ወር ባልሞላው ጊዜ ውስጥ ለገና በዓልና ለትንሳኤ በዓል በርካቶችን ደግፏል፡፡ ከ4 መቶ በላይ ለሚሆኑ ለገና በዓል፤ ከ6 መቶ በላይ ለሚሆኑ ድጋፍ ፈላጊዎች ደግሞ ለትንሳኤ በዓል ድጋፍ አድርገናል፡፡ በሬ አርደን በዓልን አብረን ውለናል፡፡


ግዮን፡- የድርጅታችሁ ራዕይ ምንድንነው?


ወንድምነው፡- የድርጅታችን ራዕይ በሀገሪቱ ትልልቅ የሥልጠና ማዕከላትን መዘርጋትና ሥራ ወዳድ፣ ሀገር ወዳድ ቢዝነስ ፈጣሪ ትውልድ መፍጠር ነው፡፡ በሀገሪቱ ላይ ትልቅ የሥልጠና ተቋም መዘርጋት እንፈልጋለን፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ችግር ፈች ትላልቅ የፋይናንስ ተቋማትን ማቋቋም እንፈልጋለን፡፡

በባንክ ደረጃ የሚታዩና በነጻነት የሚንቀሳቀሱ ተቋማትን መመሥረት ዋናው ራዕያችን ነው፡፡ ሌላው ራዕያችን የሀገሪቱን ሀብት መጠቀም የሚችል ትውልድ መፍጠር ነው፡፡ ትውልድ ጠቃሚ ትልልቅ የኢቨስትመንት ተቋማትን መፍጠር እንሻለን፡፡

በዚህ ደግሞ መንግሥትና ሕዝብ ያግዛል ብለን እናምናለን፡፡ የሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ችግር ሊፈታ የሚችል ሥራ ማከናወን እንችላለን፡፡ ይህ እንዲሳካልን ግን ሀሳባችንን የተገነዘበ መንግሥትና ሕዝብ ከጎናችን ሊቆም ይገባል፡፡


ግዮን፡- ለአሠራር አላመች ያላችሁ የመንግሥት ፖሊሲዎች አሉ?

ወንድምነው፡- እስካሁን በዚህ ደረጃ የገጠመን ነገር ባይኖርም መንግሥት ቢሠራ ብዬ የማስበው እኛን እንዲረዳን ነው፡፡ የያዝነው ሀሳብ ኢትዮጵያን ስለሚጠቅማት የሚረዳን አካል እንፈልጋለን፡፡

የሚረዳን የመንግሥት አካል ከመጣ እንደነ ኤለን መስክና መሰል ዓለም አቀፍ ቴክኖሎጂ ቀመስ ግዙፍ ባለሀብቶች የመሆን እድል ይኖረናል፡፡ የያዝነውን የሥራ ሲስተም የሚረዳ አካል ያስፈልገናል፡፡

ሀሳብ አለን፤ ሀሳባችንን ሕዝብ ተረድቶ ጥቅም ላይ እንዲውል እንሻለን፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለብዙ ሰዎች የሥራ መጠለያ ሆነናል፡፡ ስለዚህ መንግስት ሀገር የሚጠቅምና ሥራ ፈጣሪ ግለሰቦችን መደገፍና አብሮ መሥራት ይገባል፡፡


ግዮን፡- የሕብር ኢቲ አባል መሆን የሚፈልጉ አካላት ምን ይጠበቅባቸዋል?


ወንድምነህ፡- ማንኛውም ሰው የሕብር ኢቲን ፓኬጅ በመግዛት አባል መሆን ይችላል፡፡

ግዮን፡- ማስተላለፍ የሚፈልጉት መልእክት ካለ እድሉን ልስጥዎ?
ወንድምነው፡- ማስተላለፍ የምፈልገው መልዕክት ለኢትዮጵያ ሕዝብ ነው፡፡ እኔ ህብር ኢቲን ሰው እንዲያውቀው እፈልጋለሁ፡፡ መጥቶ እንዲጠይቀኝም እፈልጋለሁ፡፡

የሚገርም ሀሳብ እንዳለኝ የሚረዳኝ ሰው እሻለሁ፡፡ እኔ መንግሥትም ይሁን ሌላው አካል ይህን ሀሳቤን ተረድቶ ቢወስደው ደስ ይለኛል፡፡ አንድ የገባኝ ነገር ቢኖር ፈጠራ ምን እንደሆነ ማወቄ ነው፡፡ ፈጠራ ማለት የሌለን ነገር በመፍጠር የምንሠራው ተግባር ማለት ነው፡፡ ፈጠራ ለማምጣት አዕምሮን መቀየር ያስፈልጋል፡፡


ለአባሎቼና ለኢትዮጵያ ሕዝብ የማስተላልፈው ‹‹ስማርት ትውልድ›› እንሁን! የሚል ነው፡፡ ስማርት ማለት ሁለገብ እውቀት ያለው መሆን ማለት ነው፡፡ ለሆድና ግላዊ መሻት የሚሮጥ ትውልድ መሆን የለብንም፡፡ ሥራ ፈጣሪ ትውልድ እንድንሆን እሻለሁ፡፡ የሕዝባችን ቀልብ በፖለቲካ፣ በዘር፣ በሃይማኖት ተስቧል፡፡

ይህ ምልከታው መቀየር አለበት፡፡ እኔ በኢትዮጵያ ምድር ላይ አለፍኩበት ወይስ አለፈችብኝ የሚለውን ትርጓሜ መረዳት ያሻል፡፡ ኢትዮጵያ የዘላለም ገነት አይደለችም፡፡ ነገር ግን እኛ ባለንበት ሰዓት ምን ሠራን የሚለውን መጠየቅ ያሻል፡፡ የአእምሮ ሕግን ተጠቅሞ ቅንነትና ደግነት በተሞላበት መልኩ የሚሠራ ትውልድ እንዲፈጠር እሻለሁ፡፡


ግዮን፡- ስለነበረን ቆይታ በአንባቢያን ሥም ከልብ እናመሠግናለን፡፡

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

ጥቃት አድራሹ ከካሊፎርኒያ መሆኑን ትራፕ ገለፁ

ትናንት ቅዳሜ ምሽት በዋይት ሃውስ የጋዜጠኞች ማኅበር የእራት ግብዣ...

በኬንያ የመንገደኞች አውሮፕላን ከመስመሩ ወጥቶ ተከሰከሰ

ዛሬ ረፋድ ላይ በኬንያ ማንዴራ የአውሮፕላን ማረፊያ አንድ...

አቶ ጀማል አህመድ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ተጨማሪ 26 ሚሊየን ብር ሰጡ

አቶ ጀማል አህመድ ባሳለፍነው ወር ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ  ከሰጠው...

“የቻይና-አፍሪካ የምርምር ማዕከል”በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሊከፈት ነው

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከቻይና-አፍሪካ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር "የቻይና-አፍሪካ የምርምር...