የፌደራል የታክስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 983/2008ን ለማሻሻል የወጣው ማሻሻያ አዋጅ በርካታ መሠረታዊ ለውጦችንና አዳዲስ አሰራሮችን ይዞ ቀርቧል። ዋና ዋናዎቹ ለውጦች የሚከተሉት ናቸው፡-
- አዳዲስ ትርጓሜዎችና የተቋም ስም ለውጥ
👉🏽 መስማማት (Settlement)፡ የታክስ አለመግባባቶችን በውይይትና በስምምነት ለመፍታት የሚያስችል አዲስ አሰራር በትርጓሜ ደረጃ ተካቷል።
👉🏽 የታክስ ማጭበርበር፡ ታክስን ለመሰወር የሚደረጉ እንደ ሐሰተኛ ደረሰኝ ማቅረብና ገቢን መደበቅ ያሉ ተግባራት በዝርዝር ተተርጉመዋል።
- የታክስ አለመግባባቶችን በመስማማት የመፍታት ሥርዓት
ይህ አዋጁ ይዞት የመጣው ትልቁ ለውጥ ሲሆን፣ ክርክሮችን በፍርድ ቤት ወይም በይግባኝ ኮሚሽን ከመጨረስ ይልቅ በባለሥልጣኑና በታክስ ከፋዩ መካከል በሚደረግ ስምምነት እንዲቋጩ የሚያስችል ነው።
👉🏽 የአስማሚ ሚና፡ የታክስ ባለሥልጣኑ ነጻና ገለልተኛ “አስማሚ” በመመደብ ሂደቱን ያመቻቻል።
👉🏽 ሂደቱ፡ መስማማት የሚቻለው በታክስ ውሳኔ ላይ ቅሬታ ከቀረበ በኋላ ሲሆን፣ በዚህ ወቅት ለይግባኝ የተቀመጡ የጊዜ ገደቦች ታግደው ይቆያሉ።
👉🏽 ውጤቱ፡ የሚደረሰው ስምምነት በጽሁፍ ሆኖ በሁለቱም ወገኖች ከተፈረመ አስገዳጅና ተፈጻሚነት ይኖረዋል።
- በአዲስ ማስረጃ አቀራረብ ላይ የተጣለ ገደብ
👉🏽 ታክስ ከፋዮች የታክስ ውሳኔ ከተሰጠ በኋላ በቅሬታ ወይም በይግባኝ ወቅት አዲስ ማስረጃ የማቅረብ መብታቸው ተገድቧል።
👉🏽 አዲስ ማስረጃ ተቀባይነት ሊያገኝ የሚችለው ማስረጃው የታወቀው ከውሳኔ በኋላ ከሆነ ወይም አቅም በላይ በሆነ ምክንያት ካልቀረበ ብቻ ነው።
👉🏽 በዚህ መልክ የሚቀርብ አዲስ ማስረጃ በታክስ ዕዳው ላይ 20% ቅጣት እንዲከፈል ያደርጋል።
- የታክስ ስሌት ማሻሻያና የይርጋ ጊዜ
👉🏽 የማጭበርበር ድርጊት፡ ባለሥልጣኑ የታክስ ማጭበርበር መኖሩን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ካገኘ፣ የታክስ ስሌቱን የማሻሻያ ጊዜ (ይርጋ) እስከ 10 ዓመት እንዲራዘም ተደርጓል።
👉🏽 መደበኛው የታክስ ስሌት ማሻሻያ ጊዜ ግን በነበረበት 5 ዓመት ቀጥሏል።
- በሁኔታ ላይ የተመሰረተ የታክስ ክሊራንስ
👉🏽 የታክስ ዕዳ ያለባቸው ነገር ግን በክርክር ላይ ያሉ ወይም የክፍያ ስምምነት የፈጸሙ ታክስ ከፋዮች የንግድ ፈቃድ ለማደስ፣ በጨረታ ለመሳተፍና ብድር ለማግኘት የሚያስችላቸው “በሁኔታ ላይ የተመሰረተ የታክስ የምስክር ወረቀት” ማግኘት የሚችሉበት አሰራር ተዘርግቷል።
- የታክስ ከፋዮች ምደባ
👉🏽 የታክስ ከፋዮች ምዝገባ ኢትዮጵያ በተቀበለችው የዓለም አቀፍ የኢንዱስትሪ ምደባ ደረጃ (ISIC) መሠረት እንዲከናወንና ታክስ ከፋዮች በተለያዩ ምድቦች እንዲመደቡ ተደንግጓል።
- የቅጣት ማስተካከያዎች
👉🏽 ደረሰኝ አለመስጠት፡ የታክስ ደረሰኝ ሳይሰጥ ሲቀር የሚጣለው አስተዳደራዊ ቅጣት በእያንዳንዱ ደረሰኝ ብዛት ብር 100,000 (አንድ መቶ ሺህ ብር) እንዲሆን ተሻሽሏል።
👉🏽 የድርጅት ኃላፊዎች ተጠያቂነት፡ አንድ ድርጅት የታክስ ወንጀል ሲፈጽም የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ ወይም የፋይናንስ ኃላፊ ወንጀሉ መፈጸሙን ካወቁ ወይም ካዘዙ ተጠያቂ ይሆናሉ።
