ጋዜጠኛ ፋኑኤል ክንፉ “ማንነታቸው ካልታወቁ ሰዎች” ለማምለጥ ሲሞክር ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰበት ገለፀ

Date:

የፈንታሌ ሚዲያ መስራች ጋዜጠኛ ፋኑኤል ክንፉ “ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች” በአዲስ አበባ ከተማ “ሊፈፀምብኝ ነበር” ካለው ጥቃት ለማምለጥ ሲሞክር ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰበት ገለፀ።
ጋዜጠኛው በደረሰበት ጉዳት ሳቢያም ለመራመድ ከሶስት እስከ ስድስት ወር ሊፈጅበት እንደሚችል በባለሞያተኞች እንደተገለጸለት ተናግሯል።

ጋዜጠኛ ፋኑኤል ስለደረሰበት ጉዳት ለአዲስ ስታንዳርድ ሲያብራራ፣ ከወር በፊት ማለትም ህዳር 10/2018 ዓ.ም ስምንት ሰዓት አከባቢ “ሲቪል የለበሱ ሰዎች እንደሚፈልጉኝ” ከቤተሰብ ሰማሁ ሲል ይጀምራል።

ቀደም ሲል በፀጥታ አካላት በቁጥጥር ስር ሲውል የፀጥታ ኃይሎች በቀን መምጣታቸውን ያስታወሰው ጋዜጠኛው፣ እንደሚፈለግ ሲነገረው የአሁኑም እንደከዚህ ቀደሙ ሊሆን ይችላል የሚል ስጋት እንደገባውና አመሻሽ 12 ሰዓት ላይ በድጋሚ ለቤተሰብ በመደወል ስለሰዎቹ መጠየቁን ጠቁሟል።

ሆኖም ሰዎቹ ከአከባቢው አለመንቀሳቀሳቸውን ከቤተሰብ መስማቱን የገለጸው ጋዜጠኛ ፋኑኤል፣ “በዚህም ውጭ እንዳድር ከቤተሰብ ጋር ተነጋግረን፤ በኋላ ላይ ከምሽቱ ሶስት ሰዎቹ ከአከባቢው መሄዳቸውን አረጋገጥሁ” ሲል ስለሁኔታው አስታውሷል።

በወቅቱ “የቅርብ ጓደኛው ጋር በመሄድ ጉዳዩን እንደነገረው እና ከእሱ ጋር ማውራታቸውን ተከትሎ ገስት ሀውስ ያላቸው የሚያውቃቸው [የቅርብ ጓደኛው] ሰዎች ስለነበሩ ይሄን አማራጭ ተጠቅመህ እዛው ብታርፍ ይሻላል ብሎኝ ወደዚያው አቀናሁ” ሲል ጋዜጠኛው ገልጿል።

“ገስት ሀውሱ ጋር ከመሸ ከደረስን በኋላ እራት በልተን እንዳርፍ አመቻችተን ትንሽ ከእኔ ጋር አወራን” የሚለው ፋኑኤል የቅርብ ጓደኛቸው፣ “ተረጋጋ ጠዋት ነገሮችን እናስተካክላለን” ብሎኝ ሄደ ሲል ስለሁኔታው አስረድቷል።

ሆኖም የቅርብ ጓደኛው ከሄደ ከ50 ደቂቃ በኋላ ያረፈበት ክፍል በሩ በጣም ይደበደብ እንደጀመረ ጠቅሶ፣ በወቅቱ “ክፈት የሚል እና ሀይለቃል የተሞላበት ቃል እሰማ ነበር” ብሏል።

“በሩን በጣም እየገፉት ሲመጡ ክፍሏ ከጎን የበረንዳ ኮሪደር ያላት በመሆኑ ኮሪደሩ ጋር ሆኜ ተዘጋጀሁ” ያለው ጋዜጠኛው፣ “በወቅቱ ደብድበው ሞቶ ተገኘ ልባል እችላለሁ የሚል ስጋት አደረብኝ በዚህም አራት ሜትር አከባቢ ከሚረዝም ሁለተኛ ፎቅ ላይ ዘለልኩ” ሲሉ ተናግሯል።

አክሎም “ዘልዬ ከወደኩኝ በኋላ ልነሳ ስል ራሴን ሳትኩ ጭልም አለብኝ” ሲሉ ገልጾ፣ “ቀና ስል አጥንቴ ተሰብሯል። በአከባቢዬ ሲቪል የለበሱ ሰዎች ነበሩ። ይሄን እድል ደግመህ አታገኝም ብለውኝ ሄዱ። ከዛ ጨውኩኝ። በመኪና አፋፍሰው ሆስፒታል ወሰዱኝ።

መጀመሪያ ዳን ሆስፒታል ሄድኩ። ኤክስሬይ ተነሳሁ። ጠዋት የካቲት 12 ሆስፒታል ሄድኩ ከዛም ወደ አቤት ሆስፒታል በሪፈር ተላኩ። የተነሳሁት ሲቲስካን ነበረ ሀኪሞቹ ሲያዩት ደንግጠው ሁለት ሰርጀሪ አደረጉልኝ” ሲሉ ስለገጠመው ሁኔታ አብራርቷል።

“ከዛ በኋላ ለ20 ምናምን ቀናት ለማንም ጉዳዩን አልተናገርኩም ነበር” ያለው ጋዜጠኛ ፋኑኤል፣ ነገር ግን ጉዳዩ “ከሚዲያ ስራው ጋር የተገናኘ ነው” ብሎ እንደሚያምን ተናግሯል። 

“ከዚህ ቀደም ሁለት ጊዜ ታስሬ ነበር። ያኔም ከቤቴ ሊወስዱኝ የመጡ ሲቪል የለበሱ ሰዎች ነበሩ። እና ከሚዲያ ጋር የተገናኘ ነው። ግን ማነው ይሄን ያደረገው የሚለውን መገመት እንጂ ይሄ ነው ማለት አልችልም” ብሏል።

“ቀደም ሲል በእስር ላይ በነበሩበት ወቅት ሜክሲኮ በሚገኝው ወንጀል ምርመራ ቢሮ ስመረመር መርማሪው እንደ መደበኛ ጋዜጠኛ አይደለም የምንመለከትህ ብሎኝ ነበር” የሚለው ፋኑኤል በወቅቱ፣ “ሆነ ብለህ አጀንዳ ትቀርፃለህ። ቀርፀህም ታስፋፋለህ። ለማን እንደምትሰራ ታውቃለህ ብሎኛል” ሲል አስታውሷል።

ቀጠል አርጎም “እኔም ያለኝ ተከታይ 50 ሺህ አይሞላም። ሚሊዮን ያላቸው አሉ ለምን እኔን ታስራላችሁ ብላቸው በሰብስክራይበር እኛን ለማታለል አትሞክር። አንተ ያለህ ተከታይ አስር ሺህም ሊሆን ይችላል ግን የጣልካትን አጀንዳ የሚወስደው ሚሊዮን ተከታይ ያለው ነው አሉኝ” ብሏል።

“መንግስት መብቱ ነው ያስረሃል፣ ይጠይቀሃል፣ ይጠረጥርሃል። እኛ ደግሞ ከህግ በታች ሆነን እንሰራለን” ያሉት ጋዜጠኛው፤ “ከዚህ ውጭ ያለን መብት ግን መጠቀም ተቀባይነት የለውም” ብሏል።

አክሎም፣ “እኔ አሁን በምንም መልኩ ወደ ሚዲያ የምመለስበት ሁኔታ ያለ አይመስለኝም” ሲል ጠቅሶ፣ “እንደዚህ አይነት ነገር ክፋቱ ከቤተሰብና ጓደኛ  ዘንድ ተቀባይነት አታገኝበትም ሞራልህም ይሰበራል” በማለት ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግሯል።

በደረሰበት ጉዳት የተነሳም ለመራመድ ከሶስት እስከ ስድስት ወር ሊፈጅበት እንደሚችል ጠቁሞ ህመሙ ዕለታዊ መሆኑን እና የህመም ማስታገሻ እየወሰደ ቀኑን እንደሚያሳልፍ ገልጿል።

በኢትዮጵያ ሚዲያ ዘርፍ ውስጥ ከ15 ዓመታት በላይ ያገለገለው ጋዜጠኛ ፋኑኤል ክንፉ በሀገሪቱ ውስጥ ከሚገኙ ታዋቂ የሚዲያ ተቋማት ጋር በጋራ የሰራ ሲሆን፣ በዘገባው፣ በሚሰጣቸው አስተያየቶች እና በገለልተኛ ጋዜጠኝነት ውስጥ ባሳየው አመራር ይታወቃል።

ጋዜጠኛ ፋኑኤል ከዚህ በፊት “ሰንደቅ” በተሰኘውና በኢትዮጵያ በሳምንት አንድ ጊዜ በሚታተመው የግል ጋዜጣ ላይ በምክትል ዋና አዘጋጅነት አገልግሏል።

በመቀጠልም “ፈንታሌ ሚዲያ” የተሰኘ የኦንላይን ሚዲያ የመሰረተ ሲሆን፣ በዚህም ወቅታዊ ጉዳዮችን የሚተነትኑ የቪዲዮ አስተያየቶችን እና ትንታኔዎችን ሲያቀርብ ቆይቷል። በተጨማሪም ከዚህ ቀደም በነበረ የሥራ ዘመኑ ደግሞ “አውሎ ሚዲያ” ከተሰኘው የሚዲያ ተቋም ጋር በጋራ ሰርቷል።

በ2021 (እ.ኤ.አ) አጋማሽ ላይ ጋዜጠኛ ፋኑኤል ከሌሎች የሥራ ባልደረቦቹ ጋር በቁጥጥር ስር ከዋሉ ጋዜጠኞች መካከል አንዱ ሲሆን በኋላም በፍርድ ቤት ትእዛዝ በዋስ መለቀቁ ይታወሳል። 
   አዲስ ስታንዳርድ

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

አክሊሉ ወንድሞቹ ለንባብ በቃ

በፀሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ የልጅነት ታሪክ ላይ ያተኮረ ለታዳጊዎች...

የኢራን ተፈጥሮአዊ ምሽጎች እና ስትራቴጂካዊ ጥበብ

​ግዮን መጽሔት :- በመካከለኛው ምስራቅ የጂኦ-ፖለቲካ ትኩሳት...

ለአድዋ ድል መታሰቢያ በአሜሪካ ቀን ተሰየመ

በአሜሪካ፣ የፔንሲልቪኒያ ግዛት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ የአውሮፓዊያኑ 'መጋቢት...

ኢሎን መስክ የዓለማችን የመጀመሪያው ትሪሊዮነር ሆነ

ኢሎን መስክ የሀብት መጠኑ 1 ትሪሊዮን ዶላር ያለፈ የመጀመሪያው...