
(የአብሮነት ምሥጢር)
በአንሃኒስ ተጻፈ
በዚህ ዘመን በመሬት አቀማመጥ ወይም በአካል አጠገብ ለአጠገብ በመኾናችን ብቻ ሳይኾን በአካል እሩቅ ከምንለው ሕዝብም ጋር በቅርበት የምንኖርበት ጊዜ ላይ ነን። ከሀገራችን ርቆ ባለ ሀገር ላይ የሚከሰት ክስተት ሩቅ ብለን የምናልፈው ሳይኾን ሰምተን እኛስ ብለን የምንጠይቅበት ዘመን ነው። የአንደኛው ወገን ጥቅም ከሌላኛው ቡድን ጋር የተያያዘ ጥቅም እንዳለው ሁላችንም ልንረዳው የሚገባ ሀቅ መኾኑን እናውቃለን። በተለይ ደግሞ በአካል በቅርበት ለሚኖሩ ሕዝቦች የዕጣ መዋረስ አብዝቶ ይታያል።
የሰው ልጅ በሥልጣኔው ላለንበት ዘመን መድረሱ አንደኛው ምክንያት ማኅበራዊ መደጋገፉ ነው። ዓለም በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ ፈተናዎች የተሞላች በመኾኗ የሰው ልጅ በብዙ ፈተናዎች መካከል አልፏል። በየፈተናዎቹ ውስጥ ግን ሕልውናውን የሚቋቋም የተለያየ ተግዳሮት ሲገጥመው ነበር። የገጠመውንም ተግዳሮት ለማለፍና የሰው ዘር በምድር ለመቀጠል እርስ በርሱ መያያዝ እጅግ አስፈለጓል።
በዚህም መንገድ በአንድ አከባቢ ጦርነት ሲከሰት ወደ ሌላ ሥፍራ በመሸሽ አምልጧል። በጦርነት ጊዜ የተደበቀበት ስፍራ በሌላ ጊዜ በርሃብ ይመጣል። በዚህ ጊዜ ርሃብ ወዳልገባበት ሀገር በመሄድ እና ሕይወቱን በማቆየት ትውልዱን አስቀጥሏል። በዚህ መልክ በአደጋዎች ወቅት የሰው ልጅ ሌላኛው ወገኑ ስላለው እስከዛሬ ሕልውናውን አስጠብቆ መቆየት ችሏል። የአንደኛችን መኖር በሌላኛው ወገን መኖር ውስጥ የተመሠረተ ነውና።
የሰው ልጅ ሥልጣኔና እድገት የመጣው በፈተና ብቻ አይደለም፡፡ የሰው ልጅ አንዱ ከአንዱ ጋር በመደጋገፍ በመኖሩ ነው። አንደኛው ጋር የተትረፈረፈው ሃብት ሌላኛው ጋር በጭራሽ የለም። ያኛውም ያለው ነገር እዚህኛው ጋር ይጠፋል። በዚህ መልክ ተፈጥሮን ስንመለከታት ኾን ብላ አብረን እንድኖር የመተመሰጠረችብን ይመስላል። አንዳችን ፍላጎታችን ለመሙላት ስንል ወደ ሌላው ማኅበረሰብ እንንቀሳቀሳለን። እኛ ካለን አካፍለን ሌሎች የሌላቸውን በመስጠት ልውውጥ እናደርጋለን።
የእርስ በእርስ ልውውጥ እጅግ ጥሩ የሚኾነው በመደጋገፍ ላይ የተመሠረተ በመኾኑ ብቻ ሳይኾን በመሐል የበለጸገ ሥርዓት መፍጠር በመቻላችን ነው። በዛሬ ጊዜ በቤታችን ወይም ባለንበት አከባቢ የምንጠቀምባቸውን ቁሳቁሶች ብንመለከት በአንድ ቦታ ተሠርተው ያለቁ ሳይኾኑ ከተለያየ ቦታ የመጡ ምርቶች ናቸው። ምርቶቹ ብቻ ሳይኾኑ ምርቶች ለመመረት የበቁበት የመፍጠር አቅም የአንድ ማኅበረሰብ ብቻ አይደለም። ይልቅስ የተለያዩ ሰዎች አስተዋጽኦ ፈሶበታል።
ኢትዮጵያ ብለን ሀገራችንን በምንመለከትበት ጊዜ ነጠላ የኾነ ማንነትና ምንነት ሳይኾን በተለያየ ስብጥር የተሞላ ብዙ ግማድ አለው። ይህ መሰባጠራችን የተገኘው አንድም በአካል በቅርበት አብረን በመኖራችን ሲኾን ሁለትም በማኅበረሰባዊ መስተጋብሮቻችን የፈጠርናቸው ናቸው። በብዙ ፈተናዎች የገባነው በብዙ ዓይነት የቀለም ህብር ያበርን በመኾናችን ነው። በየጊዜ በሚገጥመን የተለያየ ተግዳሮትም በቀላሉ የማንበገረው እንዲሁ በብዙ ነገር ልንለያይ የማንችልበት ግማድ ስለገመደን ነው።
ሀገራዊ አንድነታችንን የማይወዱ አብዝተው ጥላችን በመስበክ እርስ በእርስ የማንግባባ እንድንመስል የሚፈለጉት ይህን የተያያዝነበትነን ገመድ ለማላላትና ለመበጠስ በመፈለግ ነው። አብሮ መኖርን የሚጠላ ሰው ለግሌ ኖራለሁ ቢል መሬቱን ቆርሶ አንስቶ ወዳሻው ዉቅያኖስ ማዶ ወስዶ አይኖርም። ፍላጎቱን ሁሉ በራሱ ብቻ ሞልቶ በቃኝ አይልም። ዓለም እርስ በርስ በሚኖር ግንኙነት ውስጥ እንድንኖር አድርጋ መስጠራለችና።
በአካል ቅርብ ካሉት ጋር ብቻ ሳይኾን ርቀው ካሉት ጋር ጭምር የተያያዘ ጥቅም ያለን ሕዝቦች ነን። ከሌላው ማኅበረሰብ ጋር አብሮ በመኖር የሚጠቀመው ሌላኛው ማኅበረሰብ ብቻ ሳይኾን እኛም አብረን የጥቅሙ ተካፋይ ነን። ማኅበራዊ ግንኙነት የኹለትዮሽ ጥቅም ነው። አሁን ቀናውን የሰላም መንገድ ለመከተል መንቀሳቀስ አለብን።
ቀናው የሰላም መንገድ እንደማኅበረሰብ በመደጋገፍ መኖር ነው። አንደኛው ሌላውን በጥላቻ ማንሳትና ግፍ መፈጸም የጋራ የጥፋት መንገድ ነው። ለወንድሞቻችን እና ለእህቶቻችን ርሕራሄ ያስፈልገናል። በርሕራሄ መተሳሰብ የሌሎችን ችግር ለመረዳትና ሌሎችን ለመርዳት ያስችላል። ከፍራቻ ይልቅ ፍቅር በመካከላችን እንዲበዛ አንዱ በሌላው ችግር መቆም አለበት።
የተቸገረን በመርዳት ብቻም ሳይኾን አብረን በመሥራትም ማኅበረሰባዊ መደጋገፍን ማጎልበት አለብን። አንደኛው አከባቢ ለሌሎች ካሉበት መጥተው መሥራት የሚችሉበትን እድል ሊፈጥር ይገባል። በአካባቢያችን ትልልቅ ገበያዎችን ፈጥረን ሌሎች ማኅበረሰቦችን ወደ እኛ መማረክ አለብን። ያሉንን የተለያዩ ሀብቶች ይዘን ወደ ሌሎች አከባቢዎች በመሄድ መሥራትን እናሳድግ።
ባሕልና እውቀትም የሚያድገው ሌሎችን በማስተማርና የሌሎችንም በመማር ነው። በተቀናጀ መንገድ ከሠራን ያለን እውቀት በጋራ ሰብስበን በማቀናጀት እና በማጥናት ለሀገራዊ ችግሮች ሀገራዊ መፍትሔን እንፈጥራለን። በመደጋገፍ ስንቆም የማይነቀንቁን ጠንካሮች ብቻ ሳይኾን ለመኖር ተስፋ የሚሰጥ ሕይወት መኖር እንጀምራለን። እኔ ለአንተ ተፈጥሪያለሁ፤ አንተ ደግሞ ለእኔ ተፈጥረሃል።