
እስከ አሁን ከ13 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን መዝግብያለሁ ያለው ብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም፤ በቀጣይ ሦስት ዓመታት 90 ሚልዮን ዜጎችን ለፋይዳ መታወቂያ ለመመዝገብ ማቀዱን አስታውቋል፡፡
እስካሁን ለፋይዳ መታወቂያ ከተመዘገቡት 13 ሚሊዮን ሰዎች መካከል፤ በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ 5 ሚልዮን ሰዎች መመዝገባቸው ተገልጿል።
ለእቅዱ መሳካት የምዝገባ መሳሪያዎችና የምዝገባ አጋሮችን የማስፋት እንዲሁም የተመዝጋቢ ንቅናቄን አጠናክሮ መቀጠል ይጠበቃል ተብሏል፡፡
የአገልግሎቱን ተመዝጋቢ ቁጥር ለመጨመርና ግንዛቤን ለመፍጠር የፊታችን ሚያዝያ 27፤ ከ20 ሺሕ በላይ ታዋቂ ግለሰቦችና የማኅበረሰብ ክፍሎች የሚሳተፋበት የፋይዳ ሩጫ እንደሚካሄድም ጠቁመዋል።
የብሔራዊ መታወቂያ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊ ዮዳሄ አርአያሥላሴ በአዲስ አበባ በሁሉም የሲቪል ምዝገባ ጣቢያዎች የፋይዳ ምዝገባ እየተካሄደ እንደሚገኝ አስታውሰው፤ “የአሁኑ እቅድ በአጭር ጊዜ ውስጥ በዘመቻ መልክ ምዝገባውን አካሂዶ በማጠናቀቅ መዝግቦ ጨርሶ ሲስተም ወደማስተሳሰር ለመሄድ ያለመ ነው” ብለዋል።
የፋይዳ መታወቂያ ፕሮጀክት በ2003 ዓ.ም. ለመጀመር ታስቦ የነበረ ሲሆን፤ በተለያዩ ምክንያቶች ዘግይቶ በ2010 ዓ.ም. ዳግም መንቀሳቀስ ጀምሮ በ2013 ዓ.ም. ጀምሮ ደግሞ እንደ አዲስ ተደራጅቶ ትግበራ መጀመሩ ይታወቃል፡፡
ይህም የ6 ነጥብ 6 ቢልዮን ዶላር ድረስ ቀጥተኛ የሆነ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን የሚያስገኝ ነው ተብሏል።