በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሠላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በኢንዶ ቶሺያኪ የተመራ የጃፓን የፓርላማ ልዑክ ቡድንን ተቀብሎ ውይይት አደረገ። ውይይቱ ኢትዮጵያና ጃፓን የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን በሚያጠናክሩባቸው ጉዳዮች ላይ ያተኮረ መሆኑን ከምክር ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
በውይይቱ የጃፓን ልዑክ ቡድን መሪ ኢንዶ ቶሺያኪ፤ ይህ ዓይነቱ መድረክ የቆየውን የኢትዮጵያንና የጃፓንን ወዳጅነት በተለያዩ ዘርፎች ለማጠናከርና ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሳደግ ጠቃሚ መሆኑን ገልፀዋል።
ጃፓን፤ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ሁለተኛውን ግዙፍ የሕዝብ ቁጥር የያዘችና በዕድገት ጎዳና ውስጥ ያለች ሀገር እንደመሆኗ የባሕር በር ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት እንዲሁም የዓለም የንግድ ማኅበር አባል ለመሆን ለምታደርገው ጉዞ ድጋፏ ይቀጥላል ብለዋል።
ኢንዶ ቶሺያኪ ኢትዮጵያም የሴቶችን ተሳትፎና የአስተዳደር አካል በማድረግ እየሰራች ያለችበት ሂደት የሚደነቅ መሆኑን መግለጻቸውን ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሠላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዲማ ነገዎ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያና ጃፓን የሁለቱ ሀገራት ረጅም ዓመታት በዲፕሎማሲ ፣ በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ረጅም ታሪክ ያስቆጠረ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን አስታውሰው፤ ለጋራ እድገትና ብልፅግና የሚጠቅሙ መልካም ግንኙነቶች የበለጠ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልፀዋል።
