በዲፕሎማሲ ስራወች የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም ከፍ ያደረጉ ተግባራት መከናወናቸውን እንዲሁም የኢትዮጵያ ተሰሚነት እያደገ መምጣቱን በብልጽግና ፓርቲ የህዝብ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ሃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ(ዶ/ር) ገለጹ፡፡
“መጪው ጊዜና የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዝግጅታችን” በሚል መሪ ሃሳብ የህዝብ ግንኙነት አመራሮችና ባለሙያዎችን ያሳተፈ ውይይት እየተካሄደ ነው።
በብልጽግና ፓርቲ የህዝብ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ሃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ(ዶ/ር) እንዳሉት፤ ለውጡን ተከትሎ በተሰሩ ስራዎች ህዝቡን ተጠቃሚ ያደረጉ ውጤቶች ተመዝግበዋል።
የፖለቲካ ምህዳሩ እንዲሰፋ መደረጉን ጠቅሰው፤ ህብረ ብሄራዊ አንድነትን የሚያጠናክሩ ስራዎች መከናወናቸውን አስታውቀዋል።
በማህበራዊ ዘርፍ በሰው ተኮር ስራዎች እና በጎ ፈቃድ አገልግሎቶች ላይ በጉልህ የሚታዩ ውጤቶች መገኘታቸውን አንስተዋል፡፡ በኢኮኖሚ መስክም እንዲሁ በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ምክንያት ተጠቃሽ ውጤቶች መገኘታቸውን አስታውቀዋል፡፡
የተገኙ ስኬቶችን ለህዝብ በአግባቡ ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመው፤ ከዚህ አንጻር የህዝብ ግንኙነት አመራሮችና ባለሙያዎች ወቅታዊና ትክክለኛ መረጃዎችን ተደራሽ የማድረግ ሚና ሊጠናከር ይገባል ብለዋል፡፡
የሚሰራጩ የተሳሳቱ መረጃዎች ብዥታን ከመፍጠራቸው በፊት አጀንዳዎችን ቀድሞ ተደራሽ በማድረግ መቀልበስ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የሀገር እና የህዝብ መዳረሻ ግቦች ላይ ትኩረት ያደረጉ ስትራቴጂያዊ እይታ ያላቸው ስራዎች ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባም አመልክተዋል። በተቋማት ህዝብ ግንኙነቶች መካከል በጋራና በተናበበ መንገድ መስራት ቁልፍ መሆኑንም አንስተዋል።
ወቅቱ የሚጠይቀውን የአቅም፣ የቴክኖሎጂ ዝግጅት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው፤ በዚህ ረገድ ጊዜውን የሚመጥን ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባም አስገንዝበዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡
