የዓድዋ መንፈስ አብሮን መኖሩን እያጤንን!

Date:

129ኛው የዓድዋ ድል መታሰቢያ የካቲት 23 ቀን 2017 ዓ.ም ተከብሯል፡፡ በዚህ ታላቅ የኢትዮጵያውያን አልደፈር ባይነት ተጋድሎ በተከበረበት ዕለት ደግሞ፣ መጽሔታችን ግዮን ወደ እናንተ ወደ ውድ አንባቢዎቿ መድረስ የጀመረችበት 7ኛ ዓመት መኾኑንም በዚህ አጋጣሚ ለማስታወስ እንወዳለን፡፡ በዓድዋ የድል አድራጊነት መንፈስ እና በኢትዮጵያዊ ጨዋነት የዛሬ ሰባት ዓመት ‹‹አንድ›› ብለን የጀመርናት ግዮን፣ እንኾ በብዙ ውጣ ውረዶች አልፋም ዛሬም ከእናንተ ጋር መዝለቅ በመቻሏ ትልቅ ክብርና ኩራት ይሰማናል፡፡

ይኽም ኾኖ ያለፉትንና የዘንድሮውን የዓድዋ ድል መታሰቢያ ስናከብር የግድ ልናሰናስላቸው የሚገቡ ጉዳዮች በሀገራችን ሰማይ ሥር መኖራቸው ከማናችንም የተሰወረ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ በብዙ መልኩ ማኅበረ ፖለቲካዋ ተከፋፍሎና ተበታትኖ የሚገኝበት እውነታን፣ ዓድዋ እንዴት ያርቀዋል የሚለውን አብሮ መጠየቅም ግድ እንደሚል መጽሔታችን ታምናለች፡፡ ታሪክን ላልተገቡ ርካሽ የፖለቲካ ፍላጎቶች የማዋል ተግባራት ባለፉት በርከት ላሉ ዓመታት የመጠቀም አዝማሚያዎች እየዳበረ መምጣት የዚህ ችግር መሠረት መኾኑንም ትረዳለች፡፡

እዚህ ጋር ታዲያ ለአንድ ተጨባጭ ተግባር ሕያው ምሥክርነት ሰጥቶ ማለፍ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ይኸውም በመንግሥት በኩል የድሉን ከፍታና ግርማ ሊያንጸባርቅ በሚችል መልኩ በመሃል ፒያሳ የተገነባው አዲሱ ‹‹የዓድዋ መታሰቢያ ሙዚየም›› ነው፡፡ መንግሥት ለበርካታ ዓመታት የኢትዮጵያውያን የወል አንድነት የማይፈታ ሰንሰለት ኾኖ ማገለግገል ሲኖርበት እንዲሁ በዋዛ የታለፈውን ድል በዚህ መልክ አግዝፎ የሁሉም ኢትዮጵያውያን የኩራት ምክንያት ማድረጉ የሚያስመሰግነው ነው፡፡ እግረ መንገድ ግን ዕለት ዕለት እየጠነነ የመጣውን ከኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት መንፈስ የመነጠል የትርክትና የሥነ ልቦና ባዕድነቶች በተገቢው መልኩ ለማከም ካልሞከረ ድሉም ኾነ የድሉ መታሰቢያ ሙዚየም ነፍስ የተለየው ሥጋ እንዳይኾን ያሰጋል፡፡

ይኽም ኾኖ ኃላፊነቱ በመንግሥት ላይ ብቻ የሚወድቅ ግን አይደለም፡፡ በተለያየ ጎራ ቆመው፣ በብዙ መልኩ የልዩነት ምንጭ አድርገው የተዋስዖ መድረኩን የተቆጣጠሩት ኦሮሞነት፣ አማራነት፣ ትግሬነት፣ ሶማሌነት፣ ጉራጌነትና ወዘተ የተባሉት የዛሬ ፖለቲካችን አቀንቃኞችም፣ ዓድዋ እነኚህ ማንነቶች የተረፉበት የድል ዐውድማ መኾኑን መርሳት አይገባቸውም፡፡ በዚያች የዓድዋ ምድር ደሙን በጋራ አፍሶ አጥንቱን በጋራ ያልከሰሰ ኢትዮጵያዊ የለምና፣ ዛሬ ላይ የጥንካሬያችን ሳይኾን የድክመታችን ምንጭ የመሰሉትን የእምነት፣ የቋንቋ እና የባህል ልዩነቶቻችን ከእኛ ይልቅ ቀደምት አባቶቻችን እንዴት ለተሳካ ሀገራዊ ድል እንደተጠቀሙበት መለስ ብሎ ተገቢውን ትምሀርት መውሰድ አስፈላጊ ይኾናል፡፡

በርግጥም የዓድዋ ድል ባይኖር ክርስትናችንም ኾነ እስልምናችን፣ በተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች ወስጥ የሚገኙ ድንቅ የእምነትና የባህል እሴቶችቻን አይኖሩም ነበር። እነኚህ የማንነት መኩሪያ ዕሤቶቻችን ዛሬ ደርሰው ለመገፋፋትና ለመነጣጠል ምክንያት የኾኑበት አሳዛኝ እውነታ ከመፈጠሩ በፊት፣ ሳይጠፉ ዛሬ የደረሱበትን ምሥጢር መረዳት፣ በዓድዋ የተከፈለውን ክቡር መሥዋዕትነት ግዝፈት ለመገንዘብ በር ይከፍታል፡፡

አዎን የዓድዋ ድል የተለመዱትን የዓለም የድል መዝገቦች ታሪክ ከታች ወደ ላይ ነቅንቆ በመገልበጥ ረገድ ለሌሎች አፍሪካውያን ተምኔት የሚመስል ድልን ያጎናጸፈን የታሪክ መስተዋት ነው። ሌላው ቀርቶ ዛሬ ላይ በደቡብ አፍሪካ ከዘጠና በላይ በነጮች ቁጥጥር ሥር ያለውን መሬት ዳግም በፍትሓዊነት አከፋፍሎ ጥቁር የመሬቱም የሀገሩም ባለቤት እንዳይኾን የሚሴረውን ሤራ ለሚታዘብ ማንኛውም ሰው፣ ‹‹ነጻነት›› ምን ያህል ግዘፍ የነሣ ትርጉም እንዳለው ይረዳል፡፡ እናም ኢትዮጵያውያን ከማኅበራዊ የትስስር ገጾች፣ በጠመንጃ እስከተደገፉ እንቅሰቃሴዎች፣ አልፎ ተርፎም በመንግሥት ኃላፊነት ላይ እስከተቀመጡ ሹማምንቶች ዓድዋን ስንዘክር፣ የዓድዋ መንፈስ አብሮን መኖሩን እያጤንን መኾን ይገባዋል በማለት መልዕክታችንን ለማስተላለፍ እንወዳለን፡፡

ግዮን መጽሔት ቅጽ 7 ቁጥር 223 የካቲት 29 2017 ዓ.ም

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

አርሰናል ከቦርንማውዝ በጉጉት የሚጠበቅ ጨዋታ

በ32ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ መርሐ ግብር ዛሬ ቀን...

በአሜሪካ እና ኢራን ድርድር ላይ የሚነሱ አራት ቁልፍ ጥያቄ

በፓኪስታን የሚደረገው የአሜሪካ እና የኢራን ድርድር እየተጠበበፓኪስታን ነገር ግን...

መንገዳችን ረጅም፣ ጉዟችን ፈታኝ መሆኑን እናውቃለን

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤ በዓል...

የተመድ ዋና ጸሐፊ ኢራን እና አሜሪካ “በቅን ልቦና” ወደ ድርድሩ እንዲገቡ ጠየቁ

የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ አሜሪካ እና ኢራን...