ለመጪው 7ኛው ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ የዕጩዎች ምዝገባ አከናውነውና የምርጫ ምልክቶቻቸውን መርጠው ከነበሩት 48 የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ስድስቱ በተለያዩ ምክንያቶች ከፉክክሩ ውጪ መደረጋቸውን “ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አረጋግጣለች።
ቦርዱ የድምፅ መስጫ ወረቀቶችን በውጭ አገር አሳትሞ ማጠናቀቁን ተከትሎ፣ ዘንድሮ የምርጫ ውድድሩ የሚካሄደው በተቀሩት 42 የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ብቻ እንደሚሆን ታውቋል።
ከምርጫው ውድድር ውጪ ከሆኑት ፓርቲዎች መካከል ሦስቱ መሠረታቸውን በትግራይ ክልል ያደረጉ ሲሆኑ፣ እነርሱም በትግራይ ክልል ምርጫ ባለመካሄዱ ምክንያት ከውድድር የወጡት ዲሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይ (ስምረት)፣ ትንሳኤ ሰብዓ እንደርታ እና ትንሳኤ ሥርዓት ቃንጪ ኃቂ ፓርቲዎች ናቸው።
የተቀሩት ሦስት ፓርቲዎች ደግሞ በአመራሮች የውስጥ ክፍፍልና በፍርድ ቤት ክርክር ሳቢያ ዕጩዎቹ የተሰረዙበት የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢሶዴፓ)፣ በበጀት ኦዲት ሪፖርት መዘግየት ምክንያት ምዝገባው ሳይሳካ የቀረው የሲዳማ ፌደራሊስት ፓርቲ (ሲፈፓ)፣ እንዲሁም ምክንያቱን በውል “አላውቀውም” ባለው ሁኔታ ከምርጫው የተሰረዘው እና ቦርዱን የሚወቅሰው የጋምቤላ ሕዝቦች ነፃነት ንቅናቄ (ጋሕነን) መሆናቸው ታውቋል። [ምርጫ 2018 – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር]
ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ስድስት ፖርቲዎች ከውድድር ውጪ ሆኑ
Date:
