በኢትዮጵያ ኢንሹራንስ ኢንዱስትሪው ውስጥ በርካታ ተግዳሮቶች ቢኖሩም፣ ሕብረት ኢንሹራንስ አ.ማ. በተጠናቀቀው በ2017 በጀት ዓመት ከግብር በፊት ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ ትርፍ ማስመዝገቡን አስታውቋል።
የዚህ የበጀት ዓመቱ አፈፃፀም ኩባንያዉ በታሪኩ የመጀመሪያው በቢሊዮን የሚቆጠር ትርፍ ያስመዘገበበት እንደሆነ አስታውቋል። ይህ የተነገረው ሕብረት ኢንሹራንስ ዛሬ ባካሄደው 31ኛ መደበኛ የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ነዉ።
ኩባንያው ያስመዘገበው ይህ ስኬት ባለፈው ዓመት (በ2016) ከተመዘገበው 563 ሚሊዮን ብር ያልተጣራ ትርፍ ጋር ሲነፃፀር በ79.04% ጭማሪ ማሳየቱ ተመላክቷል።
ኩባንያው ከግብር በኋላ ያገኘው የተጣራ ትርፍም ብር 843 ሚሊዮን የደረሰ ሲሆን፣ ይህም አምና ከተገኘው ብር 470.955 ሚሊዮን ጋር ሲወዳደር የ79.03% ዕድገት ማስመዝገቡን በዓመታዊ ሪፖርቱ በዝርዝር አስቀምጧል።
የሕብረት ኢንሹራንስ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ወንደሰን ተሾመ የ2017 በጀት ዓመት ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት እንደተናገሩት፣ ኩባንያው ከሕይወት ነክ፣ ሕይወት ነክ ካልሆነው (Non-Life) እና ከጀነራል ታካፉል የኢንሹራንስ ዘርፎች የሰበሰበው አጠቃላይ አረቦን ብር 2.75 ቢሊዮን ሆኗል።
ይህም አምና ከነበረው ብር 1.96 ቢሊዮን ጋር ሲነፃፀር የ40.31% ጠንካራ ዕድገት ማስመዝገቡን ሊቀመንበሩ ጠቁመዋል።
ከተሰበሰበው ጠቅላላ የአርቦን መጠን ዉስጥ 2.57 ቢሊዮን የሚሆነዉ ሕይወት ነክ ያልሆነ ኢንሹራንስ (Non-Life) ሲሆን ከ ሕይወት ኢንሹራንስ (Life) ደግሞ ከ142 ሚሊዮን ብር ገደማ መሆኑ ተገልጿል።
በተጨማሪም በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ከመድን ሥራ የተገኘው ጠቅላላ ገቢ ብር 2.33 ቢሊዮን የደረሰ ሲሆን ይህም ባለፈው ዓመት ከነበረው ጋር ሲነፃፀር የ32.20% ዕድገት እንዳለው ተመልክቷል።
ሕብረት ኢንሹራንስ ይህን ታሪካዊ ስኬት ያስመዘገበው በኢንሹራንስ ኢንዱስትሪው ውስጥ ያሉ በርካታ ተግዳሮቶችን ተቋቁሞ እንደሆነ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ወንደሰን ተሾመ በሪፖርታቸው ገልጸዋል።
በዋናነትም፣ በተሽከርካሪዎች ኢንሹራንስ ላይ ተግባራዊ እየተደረገ ያለው ቁርጥ የዐረቦን ተመን ብሎም በኢንደስትሪው አልፎ አልፎ የሚታየው ስነ ምግባር የጎደለው የንግድ ስራ እንቅስቃሴ በዓመቱ ያጋጠሙ ተጨማሪ ፈተናዎች እንደነበሩ ተናግረዋል።
