አክሽን ኤይድ ባካሄደው አዲስ ጥናት በርካታ የኢትዮጵያ መምህራንና የጤና ባለሙያዎች የገንዘብ እጥረት እየተባባሰ፣ የስራ ሁኔታ እያሽቆልቆልና ሙያቸውን ለቀው የመውጣት ፍላጎታቸው እየጨመረ መምጣቱን ገልጿል።
በሪፖርቱ መሠረት፤ የኢትዮጵያ ትምህርት ቤቶች በጀት ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ በ50 በመቶ ቀንሷል። ይህ የገንዘብ ጫና መሰረታዊ የትምህርት ቁሳቁሶች እጥረት እንዲከሰት ምክንያት ሆኗል ያለው ጥናቱ፤ በጥናቱ የተሳተፉ ሁሉም መምህራን በትምህርት ቤት መሳሪያዎች እና የመማሪያ መጽሐፍት ከፍተኛ እጥረት እንዳለባቸው ገልጸዋልብሏል። 80 በመቶ በላይ የሚሆኑት ውስን መሳሪያዎችን ከሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር ለመጋራት እንደተገደዱ ተናግረዋል።
ጥናቱ በተጨማሪም 91 በመቶ የሚሆኑት መምህራን የሥራ ሁኔታ እየተባባሰ መምጣቱን የገለጹ ሲሆን 96 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ባለፉት ከሶስት እስከ አምስት ዓመታት ውስጥ ምንም ዓይነት የሙያ ስልጠና እንዳላገኙ ተናግረዋል። እነዚህ ጫናዎች 91 በመቶ የሚሆኑት ኢትዮጵያውያን መምህራን ሙያቸውን ለመልቀቅ ፍላጎት እንዳላቸው እንዲገልጹ አድርጓቸዋል ተብሏል።
በኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ ላይ ያሉ ተግዳሮቶችም ከዚህ ያነሱ አይደሉም። በጥናቱ ከተካፈሉት የጤና ባለሙያዎች መካከል 95 በመቶ የሚሆኑት፤ የሕክምና መሳሪያዎች እና አስፈላጊ መድሃኒቶች እጥረት መኖሩን ተናግረዋል። የወሊድ ጤና ከባድ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች መኖሩን 90 በመቶ የሚሆኑት ምላሽ ሰጪዎች ገልፀዋል።
የገንዘብ ጫና ሌላኛው የጥናቱ ጭብጥ ሆኖ የተነሳ ሲሆን፣ ሁሉም የዳሰሳ ጥናት የተደረገባቸው የህክምና ባለሙያዎች ገቢያቸው በቂ እንዳልሆነ ገልጸዋል። ከሁሉም በላይ ደግሞ 75 በመቶ የሚሆኑት የህክምና ባለሙያዎች ገቢያቸው በመቀነሱ የተነሳ “የቤተሰቦቻቸውን የምግብ መጠን ለመቀነስ” እንደተገደዱ ተናግረዋል። እንዲሁም ሁሉም ምላሽ ሰጪዎች ከፍተኛ ጭንቀት እንዳለባቸው የገለጹ ሲሆን፣ ከአራቱ ሶስቱ ጤናማ የስራ እና የኑሮ ሚዛንን ለመጠበቅ እንደሚቸገሩ ተናግረዋል።
የሙያ ሥልጠና ዕድሎች አለመኖር ሌላኛው ትልቅ ችግር ሲሆን፤ 100% የሚሆኑ የጤና ባለሙያዎች ሥልጠና ማግኘት እንደማይችሉ ሪፖርት አድርገዋል። በዚህም ምክንያት 65 በመቶ የሚሆኑት ሙያውን ለመልቀቅ ያላቸውን ፍላጎት ገልጸዋል።
ጥናቱ እንዳመለከተው በሀገር አቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያ ከበጀቷ 7.1በመቶ ለጤና እና 23.01በመቶ ደግሞ ለትምህርት ትመድባለች። ሁለቱም ከዓለም አቀፍ ደረጃ በታች ናቸው ተብሏል። አገሪቱ በየዓመቱ 213.3 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት ገንዘብ በግብር ማጭበርበር የምታጣ ሲሆን፣ ከገቢዋ 6 በመቶ የሚሆነውን የውጭ ዕዳ ለመክፈል ታውላለች።
