የሩስያው ፕረዚደንት ቭላድሚር ፑቲንና የአሜሪካው ፕረዚደንት ዶናልድ ትራምፕ በአላስካ ውይይት ባደረጉበት ከሰዓታት ቆይታ በኋላ ሩስያ ሁለት የዩክሬይን መንደሮችን መቆጣጠሯን አስታውቃለች።
የሩስያ የመከላከያ ሚኒስቴር ዛሬ ባሰራጨው መግለጫ በዶኔስክ ዞን የምትገኘውን ኮሎዲያዚ እና በዲፕሮቴትሮቭስክ ዞን የምትገኘውን የቮሩን ከተሞችን መቆጣጠሩን አስታውቋል።
በዚህ ጉዳይ ላይ ከዩክሬይን መንግስት በኩል ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ የተሰጠ ማረጋገጫም ሆነ ማስተባበያ የለም።
በሌላ ዜና ዩክሬይን ሩስያ በምትቆጣጠረው የኩርሱክ ግዛት ባካሄደችው የድሮን ጥቃት አንድ አባትና ልጅ መገደላቸውን ሩስያ አስታውቃለች።
የአካባቢው አስተዳዳሪን ጠቅሶ ሮይተርስ እንደዘገበው አባትና ልጅ የሞቱት በመኪና በሚጓዙበት ጊዜ በደረሰባቸው የድሮን ጥቃት ነው።
መኪናው በዩክሬይን ድሮን እንደተመታ በእሳት መያያዙን ነው አስተዳዳሪው የገለጹት ሲሉ የዘገቡት አዣንስ ፍራንስ ፕረስና ሮይተርስ ናቸው።
