በትግራይ ክልል ሰሜን ምዕራብ ዞን አስገደ ወረዳ “ህፃፅ” ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ ለሚገኙ ተፈናቃዮች ከ257 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው ሰብዓዊ እርዳታ መሰራጨቱን የኢፌድሪ አደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።
ኮሚሽኑ በትግራይ ክልል የተፈናቃዮችን የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት በተመለከተ ባወጣው መግለጫ፤ በአሁኑ ወቅት ሰብዓዊ እርዳታ እየደረሳቸው አይደለም ተብሎ በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች የቀረበው መረጃ የተሳሳተ መሆኑን ገልጿል።
ከመስከረም እስከ ታኅሣሥ 2018 ዓ.ም ባሉት ወራት ውስጥ ለተፈናቃዮቹ ያልተቋረጠ የምግብ እርዳታ ሲደረግ መቆየቱንም ኮሚሽኑ አብራርቷል።
በዚህም መሠረት ባለፉት አራት ወራት ውስጥ 11 ሺህ 406 ኩንታል ስንዴ፣ ማሽላ፣ ጥራጥሬ እንዲሁም የምግብ ዘይት ለተፈናቃዮቹ መሰራጨቱን ኮሚሽኑ በመግለጫው ጠቁሟል።
የእርዳታ አሰጣጡም በመስከረም፣ ጥቅምት፣ ኅዳር እና ታኅሣሥ ወራት በቋሚነት በሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች ተደራሽ መደረጉን መግለጫው አመልክቷል።
ኮሚሽኑ ለተፈናቃዮች የሚላከው እርዳታ ለታለመለት ዓላማ መዋሉን የማረጋገጥ ኃላፊነት የክልሉና የአካባቢው ጊዜያዊ አስተዳደር መሆኑን አሳስቦ፤ ተጨማሪ የሰብዓዊ እርዳታ ድጋፍ የሚያስፈልግ ከሆነ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ገልጿል።
