ለኢትዮጵያ የነዳጅ ግዥ ዋነኛ መለኪያ የሆነው የብሬንት ድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ ላለፉት ሦስት ዓመታት ታይቶ በማያውቅ ሁኔታ ዳግም የ100 ዶላር ጣሪያን ተሻግሯል።
በሳምንቱ የገበያ መክፈቻ ቀን ላይ ብቻ የ15 በመቶ ድንገተኛ ጭማሪ ያሳየው የነዳጅ ዋጋ፣ በአሁኑ ወቅት በአንድ በርሜል ከ107 ዶላር በላይ እየተሸጠ ይገኛል።
የዓለም የነዳጅ ገበያ ከፈረንጆቹ 2022 የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት መባባስ ማግስት ጀምሮ በ70 እና 90 ዶላር መካከል ተረጋግቶ የቆየ ቢሆንም፣ አሁን የታየው መናር ግን ገበያውን ዳግም ወደ ባለ ሦስት አኃዝ ዋጋ መልሶታል።
ለዚህ አስደንጋጭ የዋጋ ጭማሪ በምክንያትነት የተጠቀሱት የሆርሙዝ ሰርጥ መዘጋት እና በአቅርቦት ሰንሰለት ላይ የተፈጠሩ እክሎች ናቸው። በተጨማሪም በኢራን ከፍተኛ አመራር ላይ የታየው የሥልጣን ሽግግር እና ተያያዥ የጂኦ-ፖለቲካ ውጥረቶች ስጋቱን አባብሰውታል።
የወቅቱ ቀውስ በቀጣይ ቀናትም የነዳጅ ዋጋን ይበልጥ ሊያንረው እንደሚችል እየተሰጋ ሲሆን፣ ይህም በዓለም አቀፍ የነዳጅ አቅርቦትና በታዳጊ ሀገራት ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጫና ሊፈጥር እንደሚችል ይገመታል።
