“ከሰኔ ወር ጀምሮ የቅጣት እርምጃ መውሰድ እንጀምራለን”
በአዲስ አበባ ከተማ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ብቻ ሴት አስተናጋጆች ሰውነታቸውን የሚያጋልጥ አለባበስ እንዲለብሱ የሚያስገድዱ ከ35 በላይ ሆቴሎች የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ እንደተሰጣቸው የከተማ አስተዳደሩ ባህል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ አስታውቋል።
በሆቴል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ውስጥ ተቀጥረው የሚያገለግሉ ሴት የመስተንግዶ ባለሙያዎች አለባበስን የተመለከተ መመሪያ ጸድቆ ሥራ ላይ መዋሉ ይታወሳል።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ የወጣው መመሪያ፤ ሴት የመስተንግዶ ሠራተኞች ሰውነታቸውን የሚያጋልጥ አለባበስ እንዲለብሱ የሚያስገድዱ አሰሪዎች ላይ ቅጣት የሚጥል ነው።
በቅርቡ የጸደቀው መመሪያ ተግባር ላይ ከመዋል የዘገየው የትርጉም ሥራዎች ባለመጠናቀቃቸው እንደሆነ፣ በቢሮው የቱሪስት አገልግሎት ብቃት ማረጋገጥና ደረጃ ምደባ ዳይሬክተር ገነት ይመር ለአሐዱ ተናግረዋል። በአሁን ሰዓት የትርጉም ሥራዎች መጠናቀቃቸውን የገለጹት ወ/ሮ ገነት፤ ለሆቴል አገልግሎት ሰጪዎቹ ከቅጣት በፊት ማስጠንቀቂያ እየተሰጠ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
በዚህም ባለፈው አንድ ወር ውስጥ ብቻ 35 ሆቴሎችና ሬስቶራንቶች የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ እንደደረሳቸው ገልጸዋል።
“ከቀጣዩ ሰኔ ወር ጀምሮ መመሪያው በሚያዘው መሠረት የቅጣት እርምጃ መውሰድ እንጀምራለን” ብለዋል፤ ኃላፊዋ፡፡
